ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወሳኙን ጨዋታ በአሸናፊነት አጠናቋል

ሪፖርት | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወሳኙን ጨዋታ በአሸናፊነት አጠናቋል

የአምና ሻምፒዮኖቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ወላይታ ድቻን 3-2 በማሸነፍ ቀጣይ አመት በሊጉ የሚቆዩበትን ትኬት መቁረጥ ችለዋል።

በዛሬው ዕለት  አራት ጨዋታችን ያስመለከተን የ35ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በመጨረሻው መርሐግብር የመውረድ ስጋቻ ያለበትን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፄሜ ተፈላሚው ወላይታ ድቻ ጋር አገናኝቷል። ንግድ ባንኮች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በሀድያ ሆሳዕና ከተሸነፉበት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ ሲያደርጉ ዮሐንስ ኪዳኔን በሱሌይማን ሀሚድ ሲተኩ በተቃራኒው በባህርዳር ከተማ 4-0 የተሸነፉት ወላይታ ድቻዎች ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ አዛርያስ አቤል፣ አስናቀ አምታታው፣ መሳይ ኒኮል፣ዘላለም አባተ እና ዮናታን ኤልያስን በማሳረፍ በምትካቸው ኬኔዲ ከበደ፣ ያሬድ ደርዛ፣ አብነት ደምሴ፣ተስፋዬ መላኩ እና መሳይ ሰለሞን በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

ከዚህ በፊት የተደረጉት ጨዋታዎች በዝናብ ምክንያት ዘግይተው መጀመራቸውን ተከትሎ ከተያዘለት ሰዓት 17 ያክል ደቂቃዎችን ገፋ ተደርጎ  በአ.ሳ.ቴ.ዩ ስታዲየም በዋና ዳኛ ዳንኤል ይታገሱ መሪነት ጨዋታው ጅማሮውን አድርጓል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ቢሆንም የግብ ሙከራ በማድረጉ ረገድ ድቻዎች የተሻሉ ነበሩ።

15 ኛው ደቂቃ ላይ ካርሎስ ዳምጠው ከረጅም ርቀት የሞከረው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል ሲወጣበት ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ብዙአየሁ ሰይፉ ከግብ ጠባቂ የተመለሰውን እና ወደ ግብ የመታውን ኳስ የግቡ መስመር ላይ የነበረው ኤፍራም ታምራት መልሶበታል። ከተደረገባቸው ሙከራዎች የተመለሱት ንግድ ባንኮች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 22ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ አዲስ ግደይ ወደ መሬት በማውረድ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ወደ ግብ በመምታት ድንቅ የሆነ ግብን ማስቆጠር ችሏል።

የመጀመሪያ ግባቸውን ካስቆጠሩ ከ ሶስት ደቂቃዎች በኋላ ድጋሚ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 25ኛው ደቂቃ ላይ በኋላ መስመር የተሻገረውን የአየር ላይ ኳስ ኪቲካ ጅማ እና ሳይመን ፒተር በአንድ ሁለት ቅብብል ያገኘውን ኳስ ኪቲካ ጅማ እንደ መጀመሪያው ግብ ሁሉ በሳጥኑ ጠርዝ ላይ በመምታት ድንቅ የሆነ ግብን አስቆጥሯል።

ከግቦች መቆጠር በኋላ ግቦችን አስቆጥረው ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩት የጦና ንቦቹ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።36ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳው የቀኝ ክፍል ኬኔዲ ከበደ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ካርሎስ ዳምጠው ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።

ፈጣን እና ሳቢ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ይህ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ የዳኛ ፊሽካ ሲጠበቅ ንግድ ባንኮች ሶስተኛ ግባቸውን አስቆጥረዋል። 45+3′ ደቂቃ ሳይመን ፒተር ለኤፍሬም ታምራት አቀብሎት  ከግራ መስመር ከኤፍሬም የተሻገረለትን ኳስ ራሱ ሳይመን ፒተር አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን አስፍቷል። አራት ግቦችን ያስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ራሳቸውን አሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት ወላይታ ድቻዎች የገቡባቸውን ግቦች ለማካካስ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 69ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው በዘላለም አባተ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም በግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አማካኝነት ግብ መሆን ሳይችል ቀርቷል።

ቅያሪዎችን አድርገው ደካማ ጎናቸውን ለመሸፈን የሞከሩት ድቻዎች ቅያሪያቸው ፍሬ አፍርቶ 75ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ኬኔዲ ከበደ ያሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው እዮብ ተስፋዬ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን ወደ አንድ ዝቅ አድርጓል።

ከገቡበት የመውረድ አጣብቂኝ ለመውጣት ማሸነፋቸው የግድ የሆነባቸው ንግድ ባንኮች ከዕረፍት መልስ ከተጋጣሚ ቡድን የበረታባቸውን ጫና ለመመከት የተከላካይ ተጫዋቾችን ቀይረው በማስገባት የመጨረሻዎቹን አስር ያክል ደቂቃዎች ወደ በቁጥር በዛ ብለው በራሳቸው የግብ ክልል በመከላከል የያዙትን ውጤት አስጠብቀው ጨዋታውን መጨረስ ችለዋል። ይህንንም ተከትሎ ከብዙ ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሱት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ወላይታ ድቻን 3-2 በማሸነፍ ቀጣይ አመት በሊጉ መቆየቱን አረጋግጧል።