ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ በድል ጎዳና መጓዙን ቀጥሏል

ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ በድል ጎዳና መጓዙን ቀጥሏል

ሁለቱን የሀይቅ ዳር ከተሞችን ያገናኘው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማዎች ለተከታታይ አስራ ሁለት ጨዋታዎች ያለ መሸነፍ ጉዞውን ባህርዳር ከተማን 3ለ0 በመርታት አስመዝግቧል።


የ35ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬም ሲደረጉ የዕለቱ መርሐግብር ሁለተኛ ጨዋታ ባህርዳር ከተማን ከ ሀዋሳ ከተማ አገናኝቷል። ባህርዳር ከተማዎች ወላይታ ድቻን በሰፊ የግብ ልዩነት ካሸነፉበት አሰላለፍ ምንም አይነት ለውጥ ያላደረጉ ሲሆን በተመሳሳይ ሀዋሳ ከተማዎች ወልዋሎን ሲያሸንፉ ይዘውት ከገቡት አሰላለፍ ምንም አይነት ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

9:00 ሲል በወንጂ ሜዳ የተጀመረው ጨዋታ ገና በጅማሮው ግብን ያስመለከተን ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 3ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳ የቀኝ ክፍል ላይ የተሰጣቸውን ቅጣት ምት ዓሊ ሱሌይማን ወደ ግብ ቢሞክርም ግብጠባቂው አላዛር ማርቆስ መቆጣጠር ባለመቻሉ ሲመለስ ያገኘውን ኳስ ማይክል ኦቱሉ ወደ ግብነት ቀይሮ ሀይቆቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

በኳስ እንቅስቃሴ እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረሱ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በአማኑኤል ጎበና 4ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጭ መቶ ቢሞክርም በአላዛር ማርቆስ ተመልሶበታል። 28ኛው ደቂቃ ላይ በባህርዳር ተከላካዮች በግንባር ተግጭቶ የተመለሰውን ኳስ ማይክል ኦቱሉ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ በመግጨት ለሀዋሳዎች አስቆጪ ሙከራ ሆኗል። አጋማሹ ተጨማሪ ሙከራዎችን ሳያስመለክተን በሀዋሳ 1-0 መሪነት የመጀመሪያው አጋማሽ ክፍለጊዜ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ወደ ሜዳ የተመለሱት ሁለቱ ቡድኖች ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የአጋማሹ መጀመሪያ ላይ ሀዋሳ ከተማዎች ሁለተኛ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ከኋላ መስመር መነሻውን ከብሩክ ታደለ ያደረገ እና ከተከላካዮች ጀርባ የተጣለውን ኳስ ፈጣኑ አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ግብ ጠባቂውን አልፎ ለክለቡ ሁለተኛው ለራሱ ደግሞ በውድድስ ዘመኑ 20ኛ ግቡን በማስመዝገብ በተከታታይ ዓመታት ከ20 በላይ ግብ ማስቆጠር የቻለ ብቸኛ የውጭ ዜጋ ተጫዋች መሆን ችሏል።

ሁለተኛ ግብ የተቆጠረባቸው ባህርዳር ከተማዎች ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 59ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት አምሳሉ ጥላሁን ያሻማውን ኳስ ፍቅረሚካኤል አለሙ በግንባሩ ቢገጨውም ፅዮን መርዕድ በድንቅ ንቃት ግብ ከመሆን ታድጎታል።

ድንቅ የሆነ ጊዜን እያሳለፉ የሚገኙት ሀዋሳ  ከተማዎች በተባረክ ሔፋሞ፣ ቢንያም በላይ እና ዓሊ ሱሌይማን አማካኝነት ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም በግብጠባቂው አላዛር ማርቆስ ምክንያት ጎል ከመሆን ታድጓቸዋል። 82ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም በላይ ከመሀል ሜዳ ተጫዋቾችን በማለፍ እየገፋ ይዞት የመጣውን እና ያቀበለውን ኳስ ዓሊ ሱሌይማን ለክለቡ ሶስተኛውን ለራሱ ደግሞ በጨዋታው ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል።


ጨዋታው ተጨማሪ ግቦችን ሳያስመለክተን  በሀዋሳ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።ይህንንም ተከትሎ በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት የሚመሩት ሀዋሳ ከተማዎች ተከታታይ 12ኛ ጨዋታቸውን ባለመሸነፍ ከባህርዳር ከተማ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ በማድረግ ለሶስተኝነት ያላቸውን ተስፋ አለምልመዋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የባህር ዳር ከተማው ረዳት አሰልጣኝ ደረጀ መንግሥቱ በጊዜ የተቆጠረባቸው ግብ እና የአየር ፀባዩ ያሰቡትን  እንዳያሳኩ እንዳደረጋቸው ተናግረው የመጨረሻውን ጨዋታ ውጤት አስጠብቀው ሜዳሊያ ውስጥ እንደሚገቡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት በበኩላቸው ተጫዋቾቻቸው ከጫና ውጭ ነጻ ሆነው መጫወታቸው በተሻለ ግብ ልዩነት ማሸነፍ እንዳስቻላቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።