በሊጉ ለመትረፍ ማሸነፍ፣ ከስምንት ግብ በላይ ማስቆጠር እንዲሁም የተፎካካሪዎቹ ነጥብ መጣል የሚጠብቀው አዳማ ከተማ በሜዳልያ ዝርዝር ውስጥ ለማጠናቀቅ ከሚያልመው ሀዋሳ ከተማ ጋር የሚፋለሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ እጅግ ውጤታማ ጊዜ በማሳለፍ ከወራጅ ቀጠናው ወደ ሰንጠረዡ አናት የተመነደጉት ሀዋሳ ከተማዎች ዓመቱን በድል ቋጭተው በሜዳልያ ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱበት ዕድል ለማመቻቸት አዳማ ከተማን ይገጥማሉ።
በውድድር ዓመቱ በሊጉ ከተደረጉ የአሰልጣኝ ለውጦች ውጤታማው የማን ነው ? የሚል ጥያቄ ከተነሳ “አሰልጣኝ ሙልጌታ ምሕረት” በሚል መልስ ላይ ተቋዋሚ የሚኖር አይመስልም፤ ለምን ቢባል ወልዋሎን ብቻ በልጦ በአስራ አምስት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ የነበረው ቡድን ላይ ያመጡት ተአምራዊ ለውጥ ሁሉም ስለሚያውቀው! በሀዋሳ ከተማ የወራት ቆይታቸው ካደረጓቸው አስራ ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ በ23ኛው ሳምንት በሻምፕዮኑ ኢትዮጵያ መድን ከገጠማቸው ሽንፈት ውጭ እጅ ያልሰጡት አሰልጣኝ ሙልጌታ በቆይታቸው ሰላሣ አምስት ነጥቦች በማስመዝገብ ቡድኑን ታድገውታል። ሀይቆቹ በውድድር ዓመቱ ወሳኝ ግቦችን እያስቆጠረ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑ ካስመሰከረውን ዓሊ ሱሌይማን ውጪ በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ድል አድርገው ደረጃቸውን ማሻሻልም የነገ ዋነኛ እቅዳቸው ነው።
የአዳማ ከተማ የመትረፍ ዕድል የሞተ በመሰለበት ጊዜ ቡድኑ በተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥብ አስራ አምስቱን በማሳካት በሊጉ የመቆየት ዕድሉ ማለምለም ቢችልም በመጨረሻው ጨዋታ ከፋሲል ከነማ ጋር ነጥብ መጋራቱን ተከትሎ የመትረፍ ዕድሉ እጅግ ተመናምኗል። አዳማ ከተማዎች ከሀዋሳ ከተማ ጋር በሚደረገው ጨዋታ ላይ ድል ማድረግ ብቻውን በሊጉ የመቆየት ዕድል አይሰጣቸውም፤ የቅርብ ተፎካካሪዎቻቸው ነጥብ መጣል እንዲሁም በጨዋታው ብያንስ ከስምንት ግብ በላይ ግቦች ማስቆጠር የሚጠበቅባቸው መሆኑም በሊጉ የሚቆዩበት ዕድል ጠባብ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ሰላሳ ዘጠኝ ነጥብ ሰብስቦ ለመትረፍ የሞት ሽረት ጨዋታ ከሚያደርጉት መቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ የተቀመጠው ቡድኑ የመትረፍ ዕድሉ በራሱ የሚወሰን ባይሆንም የጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ መርሐ-ግብር ከመካሄዱ በፊት የራሱን የቤት ስራ ለመጨረስ ማሸነፍ እና በርከት ያሉ ግቦች ማስቆጠር ግድ ይለዋል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ46 ጊዜያት ያህል ተገናኝተው ሀዋሳ 19 አዳማ ደግሞ 15 ጊዜ ሲያሸንፉ በ12 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ጎል በሚበረክትበት የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ ሀዋሳ ከተማ 52፣ አዳማ ከተማ 55 ጎሎችን አስቆጥረዋል።