የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንከዲሲ ዩናይትድ ጋር ባደረገው ጨዋታ እና በቆይታው ዙርያ በአሜሪካ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጆ ማሞ ምን አሉ?
በአሜሪካ በመጓዝ የኢግዚቢሽን ጨዋታውን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ሀገር ቤት ከመመለሱ አስቀድሞ አጠቃላይ ዝግጅቱን ሁኔታ አስመልክቶ የዲሲ ዩናይትድ የባለቤትነት ባለ ድርሻ የሆኑት አቶ ጆ (ኢዮብ) ማሞ ካቻ እና የፌዴሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ በጋራ በመሆን በአሜሪካ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ጆ ማሞ በዋናነት ለተጠየቁት ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የአራቱ ተጫዋቾች የሙከራ ጊዜ በምንያህል ጊዜ ይጠናቀቃል ?
“የአራቱ ተጫዋቾች የሙከራ ፕሮሰስ እንግዲህ መልማዮቹ ለአሰልጣኞቹ አቅርበዋል። አሰልጣኞቹ መጥተው ያይዋቸዋል። አንደኛ የወረቀት ሥራዎችን መጨረስ አለባቸው። ኮንትራት ከሌላቸው ካላቸው ደግሞ ከክለባቸው መውጣት እንደሚችሉ ይሄን ሳምንት ያሳውቃሉ። አቶ ባህሩ እንደነገረኝ ከሆነ አራቱም ኮንትራት የላቸውም፤ ይህ ጥሩ ነው። ግን አንድ ደብዳቤ ከፌዴሬሽኑ እንጠብቃለን ። ይህን ካገኘን በኋላ ካምፕ ይገባሉ አሰልጣኞቹ ጨዋታቸውን ያያሉ። አራቱም በአንዴ አይሄዱም። ሁለቱን አንድ ሳምንት ሁለቱን አንድ ሳምንት እንልካለን። በሁለት ሳምንት እንቅስቃሴያቸው ከተገመገመ በኋላ ዲሲ ዩናይትድ ወይም ሁለተኛ ዲቪዚዮን ሎውደን ዩናይትድ ያለው ሁሉን ነገር የሚያሳውቅ ይሆናል። ሙከራው ጥሩ ሆኖ ከተጠናቀቀ ኮንትራት የሚሰጣቸው ይሆናል። በMLS አሰራር መጀመርዩያ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ነው የሚገባው ምክንያቱም የአጨዋወት መንገዱን፣ ባህሉን ፣ አሰልጣኞቹን ማወቅ አለብህ ሦስት ወር ሁለት ወር በሁለተኛ ዲቪዚዮን ከተጫወት በኋላ ነው ወደ ዋናው ዲቪዚዮን የሚገባው። ስለዚህ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ እነዚህን ካከናወኑ እና ጠንካራ ከሆኑ ወደ ዲሲ ዩናይትድ ይገባሉ። ካልሆነም ለአንድ ዓመት ሁለተኛው ዲቪዚዮን ከተጫወቱ በኋላ ተገምግመው አንደኛ ዲቪዚዮን የመግባት ዕድል አላቸው። እኔ ባለኝ ዕውቀት እርግጠኛ የምሆነው አንድ ሁለቱ ዲሲ ዩናይትድ ይገባሉ ባይ ነኝ። ግን ፕሮሰስ አለው ይህ ደግሞ የተለመደ አሰራር ነው።”
– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያገኘው ገንዘብ መቼ ገቢ ይደረጋል ?
“ገንዘቡን በተመለከተ ቅዳሜ ነው የተጫወቱት አልፏል ቀኑ፤ እውነት ነው። በዚህ አንድ ሳምንት ውስጥ ለፌዴሬሽኑ ከዲሲ ዩናይትድ በWire ገቢ ይደረጋል።”
– ከዲሲ ዩናይትድ ወጣት ቡድን ጋር ነው የተጫወቱት ስለመባሉ ?
“ዲሲ ዩናይትድ ዋና ዋና ቡድኑን ተጫዋቾች አላሰለፈም ከወጣት ቡድኑ ጋር ነው የተጫወቱት የሚለው ጥያቄ እርሱ የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው። የቦርዱ፣ የማኔጅመት ምርጫ አይደለም። አሰልጣኙ ነው የወሰነው እነዚህን ቡድን በእነዚህ ተጫዋቾች አሸንፋለው ብሎ የፈለገውን ማድረግ ይችላል። ስለዚህ አሰልጣኙ የፈለገውን አቀረበ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሸነፈ። ደግሞም በሙሉ ወጣቶች አልተጫወቱም። ከዋናው ቡድን የገቡ ስድስት ልጆች ነበሩ። አጠቃላይ የእኛ ስህተት አይደለም የአሰልጣኞቹ ነው። መተቸት ካለበት አሰልጣኙ ነው። ስለዚህ ያለው ስጋት እንረዳለን በሚቀጥለው ዓመት ከዲሲ ዩናይትድ ጋር ግኑኝነት በማድረግ በስምምነት ጥያቄ እናቀርባለን። የተጫዋቾቹ ሁኔታ ባላንስ እንዲሆን እናደርጋለን። መናገር መብት ነው እኛ ደግሞ የመስማት ግዴታ አለብን። ነገር ሁሉም ጋዜጠኞቹም ጭምር ማወቅ ያለባቸው ይህ የአሰልጣኙ ውሳኔ መሆኑን ነው። ዓላማችን በጨዋታው ኢትዮጵያውያን የሚታዩበትን እድል ማመቻቸት ነው እርሱን አሳክተናል።”
– በቀጣይ ይህ ጉዞ በሰፊው ስለመከናወኑ
“በሚቀጥለው ዓመት አላማችን የሦስት ቀን ፕሮግራም ነው ማድረግ የምንፈልገው። ዓርብ ይጀምራል። ከስታዲየሙ ፊት ለፊት ክፍት የሆነ ትልቅ መሬት አለ እዛ ላይ የኢትዮጵያውያን ባህል የሚተዋወቅበት ሰፊ ፕሮግራም እናደርጋለን። ልብሶች ፣ ምግብና መጠጦች መዝናኛዎች በማድረግ ትልቅ የኢትዮጵያውያን ሶከር ፌስቲቫል በማድረግ እንከፍተዋለን። ቅዳሜ የሙዚቃ ኮንሰርት ይኖራል። እሁድ የጨዋታው ቀን ይሆናል ። ከጨዋታው በፊት ሙሉ ባንድ ልዩ ልዩ አርቲስቶች ይኖራሉ። ሌላው ባለፈው ዕረፍት ሰዓት ላይ እንዳያችሁት አካዳሚ ጨዋታዎች አሁን ደግሞ ከጨዋታው በፊት ሰፋ ባለ ጊዜ ከ14 ዓመት በታች የታዳጊ አካዳሚዎች እንዲጫወቱ ይደረጋል። ይህ ደግሞ አካዳሚ ውስጥ ያሉ ፈረንጆም ሆነ ትውልድ ኢትዮጵያን ታዳጊዎች እንዲነቃቁ ከወዲሁ የምንሰራ ይሆናል።”
– የጆ ማሞ አካዳሚ የመክፈት ሀሳብ
“በኢትዮጵያ አካዳሚ የመክፈት ዕቅድ አለኝ አቋቁማለው ብዬ አስባለው። ዲሲ ዩናይትድም፣ ማሞ ካቻ ፋውዴሽን ሌሎች ኢንቨስተሮች አሉ ኢትዮጵያ ላይ አካዳሚ ለመክፈት አስባለው። ከጊዜ በኋላ መሬት እንጠይቃለን። ፕላን እየሰራን ነው ረቂቅ ላይ ነው። በዕቅድ ይዘናል ግን ከ17 ዓመት በታች አካዳሚ በመክፈት ተጫዋቾችን ማብቃተወ ብቻ ሳይሆን የስፖርት ኢኒስቲትዩት በመክፍት አሰልጣኞችን የማብቃት፣ ስፖርት ህክምና፣ ስፖርት ማርኬቲንግ እና ስፖርት ጠበቆችን መማር ለሚፈልጉ ትልቅ ትምህርት ቤት አካዳሚ እንከፍታለን።