የሀገራችን ተወካይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሚያሳትፈው የሴካፋ የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ውድድር በፊት ይደረግበታል ከተባለው ሀገር ለውጥ እንደተደረገበት ይፋ ሆኗል።
ከአምስት ዓመታት በፊት ይፋ የተደረገው አህጉራዊው የሴቶች የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከዋናው ውድድር በፊት በየዞኑ የማጣሪያ ውድድሮች የሚከናወኑ ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያም በተከታታይ የሊጉ ሻምፒዮንነት ክብር ያገኘውን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲያሳትፍ ቆይቷል። ዘንድሮም ባንክ በውድድሩ ለመሳተፍ በዝውውር ራሱን አጠናክሮ ዝግጅቱ ሀዋሳ ላይ እያከናወነ ይገኛል።
ከዚህ በፊት ይህ ቀጠናዊ ውድድር በታንዛኒያ ይደረጋል ሲባል የነበረ ቢሆንም ከደቂቃዎች በፊት ከሴካፋ በወጣው መረጃ ውድድሩ ከነሐሴ 29 እስከ መስከረም 6 ድረስ በኬኒያ ናይሮቢ ከተማ እንደሚከናወን ታውቋል።
2021 ላይ የመጀመሪያውን ውድድር ያስተናገደችው ኬኒያ ዳግም የዚህን ዓመት ውድድር ለማስተናገድ ጥያቄ አቅርባ ተቀባይነት እንዳገኘችም ተገልጿል።
ዋናው የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለማለፍ በሚደረገው ውድድር የኢትዮጵያ ተወካይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ ቶፕ ገርልስ አካዳሚ (ቡሩንዲ)፣ ኬኒያ ፖሊስ ቡሌትስ (ኬኒያ)፣ ዬ ጆይንት ስታርስ (ደቡብ ሱዳን)፣ ጄ ኬ ቲ ኩዊንስ (ታንዛኒያ)፣ ካምፓላ ኩዊንስ (ዩጋንዳ)፣ ራዮን ስፖርትስ (ሩዋንዳ) እና ጄ ኬ ዩ ፕሪንሰስስ (ዛንዚባር) የሚሳተፉ ይሆናል።
በውድድሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ዬ ጆይንስ ስታርስ በአራቱም ዓመት ተሳትፎ ያደረጉና ለአምስተኛው ዓመት ውድድር ያለፉ ባለታሪክ ክለቦች ናቸው።