በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሀዋሳ ከነማን ከወራጅ ቀጠናው በማውጣት አስተማማኝ ቦታን እንዲይዝ ያደረገው አሠልጣኝ ወደ መቻል አምርቷል።
ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመራ ያሳለፈው መቻል ካቻምና በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ግን በታሰበው መንገድ ተፎካካሪ መሆን አልቻለም ነበር። የዘንድሮውን ውጤት የገመገሙት የክለቡ አመራሮች ከሙሉ የአሠልጣኝ ቡድን አባላቶቻቸው ጋር ከተለያዩ በኋላ አዲስ አሠልጣኝ ለመሾም እንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በመንበሩ አሠልጣኝ መሾማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
መቻልን ለመጪው 24 ወራት ለማሰልጠን ስምምነት ላይ የደረሰው አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ነው። የቀድሞ የሀዲያ ሆሳዕና እና ወልቂጤ ከተማ አሠልጣኝ ሙሉጌታ በዘንድሮ የውድድር ዓመት አጋማሽ ላይ የቀድሞ ክለቡ ሀዋሳ ከተማን ተቀላቅሎ ውጤታማ ጊዜ በማሳለፍ ክለቡን ከወራጅ ቀጠናው እንዲወጣ ማድረጉ አይዘነጋም።
አሠልጣኝ ሙሉጌታ በቀጣይ የራሱን የአሠልጣኝ ቡድን እንደሚያደራጅ ይጠበቃል።