በአኅጉራዊ ውድድሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉ ክለቦች የሚጫወቱበት ስታዲየም የት ሊሆን እንደሚችል ሶከር ኢትዮጵያ ፍንጭ አግኝታለች።
በቶታል ኢነርጂስ ካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያ የሚወክሉት ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ ከቀናት በፊት በወጣው የቅድመ ማጣርያ ድልድል ላይ የዛንዚባሩ ምላንዴግ እና የሊብያው አል ኢትሃድን እንደሚገጥሙ ይፋ መሆኑ ይታወቃል። ካፍ ለቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች እና ለሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ያለፉትን ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘውን አበበ ቢቂላ ስታዲየም በመፍቀዱ ሀገራችንን የሚወክሉ ክለቦች ጨዋታቸውን በዚሁ ስታዲየም ማድረጋቸውም ይታወሳል።
አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ በቀጣይ ለሚኖራቸው ቅድመ መጣርያ ጨዋታዎች የሚጫወቱበት ሜዳ የት ይሆናል የሚለው ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሰረት ክለቦቹ የሜዳቸውን ጨዋታ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ለማድረግ መታሰቡን እና አስፈላጊውን ሥራዎች ለመሥራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ሰምተናል ።
ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ የመጀመርያው የማጣሪያ መርሐግብራቸውን በሜዳቸው የሚያደርጉ ሲሆን ጨዋታዎቹም ከመስከረም 9 እስከ 11 ባሉት ቀናት እንደሚከናወኑ ታውቋል።