ሀዲያ ሆሳዕና የአንድ ተጫዋች ውል ሲያራዝም አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊግ አስፈርሟል

ሀዲያ ሆሳዕና የአንድ ተጫዋች ውል ሲያራዝም አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊግ አስፈርሟል

ነብሮቹ የአንድ ነባር ተጫዋች ውል ሲያራዝሙ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከታችኛው ሊግ አስፈርመዋል።


በሀዲያ ሆሳዕና ቤት ለመቆየት የተስማማው ተጫዋች ፀጋአብ ግዛው ሲሆን ያለፉትን ሁለት ተከታታይ የውድድር አመታትን ቆይታ ካደረገ በኋላ በድጋሚ  ለቀጣይ አንድ አመት ከነብሮቹ ጋር ለመቆየት ስምምነት ላይ ደርሷል።

ነብሮቹ በተጨማሪም አራት ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊግ ለማስፈረም ተስማምተዋል። በፕሪምየር ሊግ እንዲሁም በከፍተኛ ሊግ በተለያዩ ክለቦች በመጫወት ልምድ ያካበተው የቀድሞው የአዳማ ከተማ፣ የጅማ አባጅፋር፣ የኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ የቤንችማጂ ቡና፣ የወልቂጤ ከተማ ባሳለፍነው ውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊጉ በደሴ ከተማ በመጫወት ያሳለፈው የተከላካይ አማካይ ጄይላን ከማል ለአንድ አመት በክለቡ ጋር ለመቆየት ተስማምቷል።

ሁለተኛው ፈራሚ አቡሽ ደርቤ ነው። የቀድሞው የሀላባ ከተማ እና ዘንድሮ በከፍተኛ ሊጉ በደሴ ከተማ ቆይታ የነበረው የመስመር አጥቂው ቀጣይ አንድ አመት በፕሪምየር ሊጉ በነብሮቹ ቤት የምንመለከተው ተጫዋች ነው።

ሦስተኛው አዲስ ፈራሚ ተጫዋች ተፈራ አንለይ ሲሆን ከዚህ በፊት በፕሪምየር ሊግ ከለገጣፎ ከተማ ጋር ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ በከፍተኛ ሊግ ለሸገር ከተማ እና ዘንድሮ በደሴ ከተማ ጥሩ የውድድር አመት ማሳለፍ ችሏል። ለአንድ አመት በነብሮቹ ቤት ለመቆየትም ተስማምቷል።

ሌላኛው ፈራሚ ተስፋሁን ሰቦቅስ ከእንጅባራ ከተማ በአንድ አመት ውል ወደ ነብሮቹ ስብስብ ለመቀላቀል ስምምነት ላይ ደርሷል።