👉 “ቡድናችን ዋንጫዎችን የሚጠግብ ቡድን አይደለም።”
👉 “ባለው አጋጣሚ ሁሉ አሸናፊ ለመሆን የሚከፈለውን መስዋዕትነት በሙሉ ለመክፈል ዝግጁ ነን።”
👉 “ከፊት ለፊታችን ለሚጠብቀን አህጉራዊ ውድድር ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን።”
👉 “አዲስ የመጡት ልጆች ትልቅ አቅም ይዘው የቡድኑን ጥንካሬ ለመጨመር ነው የመጡት።”
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒየን በመሆን በኬንያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ውድድራቸውን ሐሙስ ነሐሴ 29 የሚጀምሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከትናንት በስቲያ ሌሊት ወደ ኬንያ ጉዟቸውን ያደረጉ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም ከቡድኑ ግብ ጠባቂ እና አምበል ከሆነችው ታሪኳ በርገና ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።
ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የሴቶች ሲቲ ካፕ ውድድር ቡድናችሁን ለመፈተሽ ምን ያክል አግዟችኋል?
“ለኛ ትልቅ ግብዓት ነው የሆነልን ከዚህ በፊት በዝግጅት ወቅት የወዳጅነት ጨዋታወችን የምናደርገው ከወንዶች ቡድን ጋር ነበር አሁን ግን በዚህ ውድድር በደንብ ራሳችንን እንድንፈትሽ አድርጎናል። ውድድሩን ማሸነፍ ባንችልም ከፊት ለፊታችን ለሚጠብቀን አህጉራዊ ውድድር ትኩረት አድርገን እየሰራን እንገኛለን።”
አዲስ ከፈረሙት የውጭ እና የሀገር ዉስጥ ተጫዋቾች ጋር ምን ያክል ተዋህዳችኋል?
“አዲስ የመጡት ልጆች ትልቅ አቅም ይዘው የቡድኑን ጥንካሬ ለመጨመር ነው የመጡት እና ያለችን ጊዜ ምንም አጭር ብትሆንም በጥሩ ሁኔታ መግባባት ችለናል።”
ከውድድሩ ምን እንጠብቅ?
“ዓምና የዚህ ውድድር አሸናፊ ነበርን ቡድናችንም ዋንጫወችን የሚጠግብ ቡድን አይደለም ባለው አጋጣሚ ሁሉ አሸናፊ ለመሆን የሚከፈለውን መስዋዕትነት በሙሉ ለመክፈል ዝግጁ ነን። እዚህ የደረስነው በብዙ ፈተናወች ዉስጥ አልፈን ነው አሁንም ቢሆን ማድረግ ያለብንን በሙሉ አድርገን የክለባችንን ብሎም የሀገራችን ስም ከፍ አድርገን ለማስጠራት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን።”