የዋልያዎቹ አለቃ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ስለቀጣይ ቆይታቸው እና የብሔራዊ ቡድኑ የሽንፈት ምክንያት ምን እንደሆነ ምን አሉ?

የዋልያዎቹ አለቃ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ስለቀጣይ ቆይታቸው እና የብሔራዊ ቡድኑ የሽንፈት ምክንያት ምን እንደሆነ ምን አሉ?

👉 “በአስር ሺህ እና በአምስት ሺህ ኪሎ ሜትር ሩጫ የምንታወቅበት ነገር አለ።”

👉 “ነገ ምን እንደሚሆን ጊዜው ሲደርስ ነው የምናየው።”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከጊኒ ቢሳው እና ቡርኪና ፋሶ ጋር ለሚያደርጋቸው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ያደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ዛሬ በፌዴሬሽን የመሰብሰብያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ከተነሳባቸው ጥያቄዎች መካከል ከፊታቸው ያሉ ሁለት የምድብ የመጨረሻ ጨዋታ ካደረጉ በኋላ ይቆያሉ ወይስ ይህ ጨዋታ የመጨረሻዎ ነው ተብለው ሲጠየቁ ተከታዩን ምላሽ ብለዋል።

“ከቆይታ ጋር በተገናኘ እንግዲህ እግዚአብሔር የፈቀደው ነው በሰው ሕይወት ውስጥ የሚሆነው። ነገ ምን እንደሚሆን ጊዜው ሲደርስ የምናየው ይሆናል።” በማለት በአጭሩ የመለሱ ሲሆን በማስከተል የብሔራዊ ቡድን ሽንፈት መብዛት ምክንያቱ ምንድነው ተብለው ተጠይቀው ሲመልሱ

“ምንድን ነው የብሔራዊ ቡድኑ ድክመት የሚለውን በአንዴ ይህን በዚህ ሚዲያ ላይ ብቻ ተናግረን ያበቃል ብዬ አላስብም። ግን አንዳንዴ ረጅም ጊዜ ላይፈልግ ይችላል ብዬ አስባለው። በትክክል ብናጠና እና ብንመረምር ምንድን ነው ከእኛ ጋር ሊያስኬደን የሚችለው ጨዋታ ምንድን ነው የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል። ጊዜ ይፈልጋል ማስተካከል መታረም ያለባቸውን ነገሮች አሉ ብዬ አስባለው። ግን ብዙ ባለ ድርሻ አካላት ፣ ሚዲያውን ፣ መንግስትን ጨምሮ ክለቦች ብዙ ነገሮች አሉ ያ ተጠንቶ ለሆነች መድረክ ሳይሆን በደንብ ሰርተን ለማረም መስራት አለብን ብዬ አስባለሁ። ሆኖም ከራሳችን ሙያ አንፃር መታረም ያለባቸው የምለው እኛ ካለን ነገር አንፃር በከፍተኛ ፕሬሲንግ ተጭነን ብንጫወት ኳሱን ስናገኝ ብቻ ሳይሆን ኳሱን ስናጣ ጫና ፈጥረን ብንጫወት ያው በአስር ሺህ በአምስት ሺህ ኪሎ ሜትር ሩጫ የምንታወቅበት ነገር አለ እነርሱ በአጭር ኳስ ይታወቃሉ ይህን ቀላቅለን እንዴት ነው መተግበር ያለብን እግርኳሱ ምንድነው የሚፈልገው ብለን ብናደርግ፣ ብንሰራ በትላልቅ መድረኮች በአጭር ጊዜ ውስጥ አገራችንን ማስጠራት እንችላለን።”