የኢትጵያ ስፖርት አካዳሚ ያዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና ተጀመረ

የኢትጵያ ስፖርት አካዳሚ ያዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና ተጀመረ

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የእግር ኳስ እና አትሌቲክስ አሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ጀመረ።

የስፖርት አካዳሚው ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ ማሰልጠኛ ማዕከላት እና ለዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚዎች የእግር ኳስ እና አትሌቲክስ አሰልጣኞች ከጥቅምት 10-12 ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የተግባር እና ንድፍ ሀሳብ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

ስልጠናውን በይፋ ያስጀመሩት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ መክዩ መሀመድ “አሸናፊ ሀገርን ለመገንባት ስፖርትን እንደ አንድ መሳሪያ መጠቀም አለብን ለዚህም ብቁና ተወዳዳሪ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የአሰልጣኞችን አቅም ማጎልበት ዋናው ነው:: ለዚህም አካዳሚው፣ ማሰልጠኛ ማዕከላት እና የዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚዎችን አቀናጅተን በቅብብሎሽ ወጥ ስልጠና ለመስጠት የአሰራር ስርአት እንዘረጋለን” ሲሉ ሀሳባቸውን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አምበሳው እንየው ባስተላለፉት መልዕክት “ስፖርትን ለማሳደግ ስልጠና ወሳኝ ነው በተለይ ምልመላ ፣ተሰጥኦ ልየታ፣ የስፖርት ግብ አጣጣል፣ምዘና እና ሌሎችንም የስፖርት ቴክኒካል ጉዳዮች ከማሰልጠኛ ማዕከላት እና ከዩኒቨርሲቲ አካዳሚዎች ጋር በቅንጅት እንሰራለን” ብለዋል።

ስልጠናው እስከ ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም በእግርኳስ እና አትሌቲክስ ስፖርቶች በተግባር እና በንድፈ ሀሳብ ታግዞ ይሰጣል።