የአቤል ያለው ብቸኛ ግብ ፈረሰኞቹን ሦስት ነጥብ አስገኝታለች

የአቤል ያለው ብቸኛ ግብ ፈረሰኞቹን ሦስት ነጥብ አስገኝታለች

በአዲስ አበባ ስቴድየም በተካሄደ የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የምድብ ሁለት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገሌ አርሲን አሸነፈ።

ፈረሰኞቹ ብልጫ የወሰዱበት የመጀመርያው አጋማሽ ማራኪ እንቅስቃሴና በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረጉበት ሲሆን አዲሱ አቱላ ከቆመ ኳስ አሻግሮት ዳዊት መለሰ ወደ ራሱ ግብ ከማስቆጠሩ በፊት ኢድሪሱ አብዱላሂ ደርሶ ወደ ውጭ ያወጣው እንዲሁም ቢንያም ፍቅሬ ከቀኝ መስመር አሻግሮት ፍፁም ጥላሁን ያመከነው አስቆጪ ሙከራዎች ፈረሰኞቹም መሪ ለማድረግ ተቃርበው ነበር። ቶሎሳ ንጉሴ ከቀኝ መስመር አሻግሮት አቤል ያለው በግንባሩ ገጭቶ ኢድሪሱ በድንቅ ብቃት ያወጣው እንዲሁም ፍፁም ጥላሁን ያደረገው ሙከራም ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በመከላከል ተጠምደው የነበሩት ነገሌ አርሲዎችም ዳግማዊ አርዓያ ከቆመ ኳስ መቶት ፋሩክ ሺካሎ ወደ ውጭ ባወጣው እንዲሁም ገብረመስቀል ዱባለ ባደረገው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር።

ፈረሰኞቹ ብልጫቸውን ያስቀጠሉበት ሁለተኛው አጋማሽ ብርቱ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን አዲሱ አቱላ ከርቀት አክርሮ ያደረገው እንዲሁም ቢንያም ፍቅሬ ከቆመ ኳስ አክርሮ መቶት በእድሪሱ አብዱላሂ የተመለሱ ሁለት ሙከራዎችም ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በ77ኛው ደቂቃ ግን አቤል ያለው በዳዊት መለሰ የቅብብል ስህተት ያገኛትን ኳስ ግብ ጠባቂውን አታሎ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ፈረሰኞቹ ከግቧ በኋላም ፍፁም ጥላሁን ከርቀት ባደረጋት ሙከራ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በርካታ ሙከራዎች የተደረጉበት እንዲሁም ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አብዱላሁ ድንቅ ብቃት ያሳየበት ጨዋታም በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል።