በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዳማ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕናን ያገናኘው የ3ኛ ሳምንት የምድብ ሁለት መጠናቀቂያ ጨዋታ ለተመልካች ሳቢ እንቅስቃሴ ሳያስመለክት ያለ ጎል ተጠናቋል።
09፡00 ሲል በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት የተጀመረው የምድብ ሁለት የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በሙከራዎች ያልታጀበና ሳቢ እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ነበር። ሁለቱም ቡድኖች ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባደረጉበት አጋማሽም የመጀመርያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ተመስገን ብርሃኑ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ሞክሮት ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ በእግሩ መልሶ ካወጣበት ብቸኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ አልተደረገበትም።

ከዕረፍት መልስም በተመሳሳይ አሰልቺና በሙከራዎች ሳይታጀብ ቀጥሎ አንድም የሚጠቀስ ያለቀለት የግብ ዕድል ሳይፈጠር ጨዋታው ባዶ ለባዶ ተጠናቋል። ውጤቱ ለአዳማ ከተማ ከሦስት ጨዋታዎች ሦስተኛ የ0-0 ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል። ሀዲያዎች በአንጻሩ ከሦስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ማሳካት ችለዋል።



