በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጨዋታዎች ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-1 ሲለያዩ መቻል እና ፋሲል ከነማ ያለግብ ተለያይተዋል።
ሀዋሳ ከተማ 1-1 ኢትዮጵያ ንግድ
በአምስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታ በምድብ ሁለት 9:00 ሲል በሀዋሳ ስታዲየም ሀዋሳ ከተማን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገናኝቷል። ሁለቱን ከድል የተመለሱ ቡድኖችን ያገናኘው ይህ ጨዋታ ጥሩ የሚባል የኳስ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ሲሆን 27ኛው ደቂቃ ላይ ተባረክ ኤፋሞ ያቀበለውን ኳስ ታዳጊው ያሬድ ብሩክ ከሳጥን ውጭ በመምታት ግብ አስቆጥሮ ሀይቆቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ግቡን ካስቆጠረ በአንድ ደቂቃ ልዩነት ያሬድ ብሩክ ከጌታነህ ከበደ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ መቶት የግቡ ማዕዘን የመለሰበት ኳስ ለሀይቆቹ አስቆጪ ሙከራ ነበር።

ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ አግብተው ወደ ጨዋታ ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች 38ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ባስቆጠረው የቅጣት ምት ግብ ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ አቻ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎችን ሀያ ያክል ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 64ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም አበበ ከያሲን ጀማል የተቀበለውን ኳስ ብቻውን ይዞ ከግብ ጠባቂ ጋር መገናኘት ቢችልም ግብጠባቂው ሀብታሙ ሰይድ ግብ ከመሆን ታድጎታል። ጨዋታውም 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
መቻል 0-0 ፋሲል ከነማ
ምሽት 12 ሲል በሀዋሳ ዩኒቨርሲት ስታዲየም የሊጉ አናት ላይ የተቀመጡትን መቻል እና ፋሲል ከነማን ያገናኘ ሲሆን 8ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ከ አብዱልከሪም ወርቁ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ግብ የሞከረው ሲሆን በግብጠባቂው ሞየስ ፓዎቲ ጥረት ግብ ከመሆን ታድጎታል። በፋሲል ከነማ በኩል16ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

በተደጋጋሚ የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል መጎብኘት የቻሉት ዐፄዎቹ 29ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ያሬድ ብርሃኑ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረው ኳስ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበታል። በአጋማሹም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ ሳያስመለክቱን ወደ ዕረፍት አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ረዘም ያሉትን ደቂቃዎች ያለ ሙከራ ያስመለከተን ሲሆን በአጨዋወት ረገድ ፋሲል ከነማዎች ኳስን ከራሳቸው የግብ ክልል መስርተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ ጫናን ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 84ኛው ደቂቃ ላይ በኪሩቤል ዳኘ እና በረከት ግዛው አማካኝነት ተከታታይ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ግብ ጠባቂው መልሶባቸዋል። ውጥረት በበዛበት በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ውስጥ መቻሎች 88ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ደስታ አማካኝነት ያለቀለት የግብ ሙከራ ቢያደርጉም ግብጠባቂው ሞየስ ፓዎቲ እንደምንም ብሎ ወደ ውጭ አውጥቶታል። ጥሩ የኳስ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።



