ቡርኪናቤው ምዓም አናብስትን ለመቀላቀል ተስማማ

ቡርኪናቤው ምዓም አናብስትን ለመቀላቀል ተስማማ

መቐለ 70 እንደርታዎች ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ከስምምነት ደርሰዋል።

ካከናወኗቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት የአቻ ውጤቶች እና ሦስት ሽንፈቶች በማስተናገድ በሁለት ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት በአሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት የሚመሩት መቐለ 70 እንደርታዎች የቡርኪናፋሶ ዜግነት ያለው ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ተስማምተዋል። ክለቡን ለመቀላቀል የተስማማው ተጫዋች ደግሞ መሐመድ ዜጉ ትራኦሬ ነው። ከዚህ ቀደም በሀገሩ ክለቦች ‘IFFA Matourkou’ ፣ ‘US des Forces Armées’ ፣ ‘ASEC Koudougou’ እንዲሁም በኮትዴቭዋሩ SOL FC d’Abobo መጫወት የቻለው ይህ ወጣት ግብ ጠባቂ ያለፉትን አራት ዓመታት በቡርኪናፋሶው ‘Faso Foot Ligue 1’ ተሳታፊ ለሆነው ኤ ኤስ ዶዋነስ በመጫወት የቆየ ሲሆን ክለቡ የሱፐር ኮፓ አሸናፊ በሆነበት 2024 የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ  ክብር አሳክቷል።

በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ለቡርኪናፋሶ ወጣት እና ዋናው ቡድን መጫወት የቻለው ይህ ተጫዋች መቐለ 70 እንደርታን ለመቀላቀል መስማማቱን ተከትሎ ዛሬ አመሻሽ አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም በይፋ ፊርማውን ያኖራል።