ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች|  የ18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ18ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

የ18ኛ ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ይጀምራሉ። የዕለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችንም እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

ሽረ ምድረገነት ከ ኢትዮጵያ መድን

 

አርባምንጭ ከተማን ካሸነፉ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ግብ የተለያዩት ሽረ ምድረገነቶች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግብ አለማስተናገዳቸው ጠንካራ ጎናቸው ነው። ሆኖም ግን በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በኩል በተለይም በሁለተኛ አጋማሽ በብዛት የሚስተዋልባቸውን መቀዛቀዝ መቅረፍ ይኖርባቸዋል። እንደሚፈጥሯቸው የግብ ዕድሎች ያለባቸው የአጨራረስ ችግር በ17 ጨዋታዎች 13 ጎሎችን ብቻ እንዲያስቆጥሩ አድርጓቸዋል። በዛሬው ዕለትም ተጋጣሚያቸው ድልን አብዝቶ ከመናፈቁ የተነሳ አቀራረቡ ፈታኝ ሊሆን ስለሚችል በሁሉም ቦታዎች ትኩረት የተሞላበት እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ከተከታታይ 0ለ0 ውጤቶች በኋላ በመቻል 1ለ0 የተሸነፈው ኢትዮጵያ መድን የዘንድሮ ጉዞው እጅግ ፈታኝ ሆኖበታል። ከመጨረሻ ስምንት ጨዋታዎች በአራቱ ተሸንፎ ፣ በሦስቱ አቻ ተለያይቶ በአንዱ ብቻ ድል ያደረገው ቡድኑ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ እያጣው ያለውን ጥንካሬ መመለስ የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ዋነኛ ሥራ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በመጨረሻ 3 ጨዋታዎች ጎል የራቀው የማጥቃት አደረጃጀቱ ወደ ግብ ማስቆጠር ተመልሶ በራስ መተማመኑን መመለስ ይኖርበታል። ባለፈው የውድድር ዓመት በአጠቃላይ ባደረጋቸው 34 ጨዋታዎች 15 ጎሎችን ብቻ ያስተናገደው የተከላካይ መስመሩም በያዝነው የውድድር ዓመት ገና በ17ኛ ሳምንት በተመሳሳይ 15 ግቦችን ማስተናገዱም አንዱ የቡድኑን የወደፊት ጉዞ ከባድ እንደሆነ የሚጠቁም ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን በመጀመሪያው ዙር 3ለ1 ፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 3ለ0 ማሸነፍ ችሏል።

 

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

 

ነጌሌ አርሲ ላይ ወሳኝ ድል ካሳካ በኋላ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ያለ ግብ የተለያየው ሀዋሳ ከተማ በዚሁ ጨዋታ ላይ ተዳክሞ የቀረበ ሲሆን ከአቻ ውጤቱ በኋላም በ 29 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ የተቆጠረበት እና ትኩረት የሚስብ ጠንካራ የመከላከል ክፍል ያላቸው ሐይቆቹ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ አልፎ አልፎ የሚታይባቸውን ተደራጅቶ ወደ ሳጥን የመግባት ችግር ከቀረፉ ከዚህም በላይ ሊጓዝ የሚችል ቡድን መገንባታቸው በግልጽ ይታያል።

ከመጨረሻ 10 ጨዋታዎች በስድስቱ አቻ ተለያይተው በሁለቱ ተሸንፈው በሁለቱ ድል ያደረጉት ኤሌክትሪኮች እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ በሊጉ ሰንጠረዥ መሪ ሊያደርጋቸው ወይም ይበልጥ ሊያፎካክራቸው የሚችለውን ዕድል በተደጋጋሚ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በተለይም በእነዚህ ጨዋታዎች 5 ጎሎች ( በሁለት ጨዋታ አንድ ጎል ) ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ኃይል ይበልጥ መሻሻል ይኖርበታል። ከፍ ባለ ተነሳሽነት ሙሉ ደቂቃ በመጫወት የሚታወቀው ቡድኑ ይህንን እንቅስቃሴ ካለበት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርሰው ውጤት ያስፈልገዋል።

ቡድኖቹ በሊጉ 44 ግንኙነቶች ሲኖራቸው ኤሌክትሪክ 18 ፣ ሀዋሳ 15 ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገዋል። 11 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ኤሌክትሪክ 66 ፣ ሀዋሳ ደግሞ 50 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

 

ወላይታ ድቻ ከ አዳማ ከተማ

 

ከመጨረሻ 7 ጨዋታዎች በሁለቱ ተሸንፈው በአምስቱ አቻ የተለያዩት የጦና ንቦች ቀስ በቀስ ራሳቸውን አጣብቂኝ ውስጥ ከትተው አርባምንጭን ብቻ በልጠው 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድኑን ሲረከቡ ከፍተኛ መሻሻል እና ተስፋ የታየ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ የቡድኑ እንቅስቃሴ በተለይም የማጥቃት አደረጃጀቱ ትልቅ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። ከቀናት በፊት ሴኔጋላዊ ግብ ጠባቂ ያስፈረመው ቡድኑ የተዳከመውን የኋላ መስመር እንዲያሻሽል ጥሩ ዘዴ የዘየደ ቢመስልም አሁንም ግን ባሳለፍነው ሳምንት እንደጠቀስነው ከሚፈጠሩ የግብ ዕድሎች አንጻር እጅግ ደካማ በሆነ አጨራረስ እየባከኑ ያሉ ዕድሎችን የሚጠቀሙበት መንገድ ላይ በደንብ መሥራት አለባቸው።

ወደ መቀመጫ ከተማቸው ካመሩ በኋላ ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፈው በሁለቱ አቻ የተለያዩት አዳማ ከተማዎች በተለይም በመጨረሻው ሳምንት ከመቐለ ጋር ባደረጉት ጨዋታ አንድ ብቻ ዒላማውን የጠበቀ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረጋቸው ደጋፊዎችን አላስደሰተም ነበር። በዚሁ ጨዋታ ግብ አያስተናግዱ እንጂ ካለፉት አራት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ያስተናገደው የተከላካይ መስመሩ ግቦች በቀላሉ የማይቆጠሩበት ቡድን ሆኖ ከመቆየቱ አንጻር እንደ መቀዛቀዝ ቢቆጠርም እነዚሁ ተከላካዮች የማጥቃት እንቅስቃሴውን ማገዛቸው ጥሩ ጎናቸው ነው። ሆኖም ከመሪው ሲዳማ ቡና ጋር ያላቸውን የ6 ነጥብ ልዩነት ለማጥበብ አልያም ባለበት አቆይቶ የመጀመሪያውን ዙር ለማጠናቀቅ በደጋፊዎቹ ፊት የመጫወት ዕድሉን ተጠቅሞ ተከታታይ ድሎችን ማሳካት ይኖርበታል።

ቡድኖቹ 22 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ 9 በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ 7 ጨዋታ አሸንፏል። ቀሪው 6 ጨዋታ ደግሞ አቻ ተጠናቋል። ወላይታ ድቻ 24፣ አዳማ 20 ግቦች አስቆጥረዋል። (የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አልተካተተም