ሪፖርት| ሽረ ምድረ ገነት  እና ኢትዮጵያ መድን ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| ሽረ ምድረ ገነት እና ኢትዮጵያ መድን ነጥብ ተጋርተዋል

ሽረ ምድረ ገነት እና ኢትዮጵያ መድንን ያገናኘው ጨዋታ 0 – 0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

 

የዕለቱ የአዲስ አበባ ስታድየም ብቸኛ መርሐ ግብር  በነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በእንቅስቃሴ እና በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ኢትዮጵያ መድኖች የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሶ አደጋዎችን በመፍጠር ረገድ ግን ሽረ ምድረ ገነቶች ብልጫ ነበራቸው። ገና በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ሽረ ምድረ ገነቶች ከማዕዘን ምት በተሻማው እና አቤል ብርሃነ በግንባሩ ገጭቶት ለጥቂት በግቡ አግዳሚ በወጣበት አጋጣሚም የመጀመሪያውን ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ኢትዮጵያ መድኖች በበኩላቸው 8ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳው የመሀል ክፍል ላይ የተሻገረውን እና አለን ካይዋ በደረቱ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ብሩክ ሙሉጌታ ለግብ ጥሩ አቋቋም ላይ ሁኖ ወደ ግብ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው ሪችሞንድ አይ እንደምንም ብሎ ወደ ውጭ አውጥቶበታል።

11ኛው እና 28 ደቂቃ ላይ አቤል ማሙሽ ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ አክርሮ የመታቸውን ተመሳሳይ ኳሶች ከረጅም ወራት ጉዳት በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በድንቅ ጥረት ግብ ከመሆን የታደጋቸው ኳሶችም በሽረ ምድረ ገነት በኩል የተደረጉ ተጨማሪ ሙከራዎች ናቸው። በድጋሚ 19ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ማሙሽ ከሽመክት ጉግሳ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ በግራ እግሩ አክርሮ መቶት የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰ ኳስም ሽረዎችን መሪ ለማድረግ የተቃረበ አጋጣሚ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ መድኖች ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ እና የተሻሉ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉበት ቢሆንም አጋማሹ በርከት ያሉ የጠሩ የግብ ሙከራዎች አልተደረገበትም። 83ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት አውላቸው ከሳጥን ውጭ ተጫዋች አልፎ በግራ እግሩ የመታው እና ግብ ጠባቂው ሪችሞንድ አይ ግብ ከመሆን የታደገው ኳስም በአጋማሹ የተሻለው ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። በአዲስ አበባ ስታድየም የተካሄደው ጨዋታም ያለ ግብ 0 – 0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።