ሁለት ድንቅ ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ 1ለ1 ተያይተዋል።

በአዳማ የተካሄደ የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ብልጫ የወሰዱበት እንዲሁም በርከት ያሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር።
በማጥቃቱ ረገድ ብልጫ የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች ብርሀኑ በቀለ ከመስመር አሻግሮት መሳይ አገኘሁ በአግባቡ ያላራቀውን ኳስ አግኝቶ ብሌስ ናጎ ከግቡ ቅርብ ርቀት ሆኖ ባደረገው ሙከራ ጥቃታቸው ከጀመሩ በኋላ ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ፍራኦል መንግስቱ ከመሀል ሜዳ እየገፋ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶት የግቡን ቋሚ የመለሰው ኳስ እንዲሁም ፍራኦል መንግስቱ ከቆመ ኳስ አሻምቶት ብርሀኑ በቀለ ከመታው በኋላ ፔፔ ሰይዶ መልሶት ቋሚውን ገጭቶ የተመለሰው ኳስ ደግሞ ሲዳማ ቡናዎችን ቀዳሚ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። ክዋቤና ቧቲንግ በረዥሙ ተሻግራ ወንድወሰን በለጠ በግንባሩ የጨረፋትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ ደግሞ በባህር ዳር ከተማ በኩል የምትጠቀስ ሙከራ ነች።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተለየ ተመጣጣኝ ፉክክር የተደረገበት ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ነበር። አናንያ ጌታቸው በጥሩ መንገድ የተሰነጠቀችለትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ኢማኑኤል ካል ያዳናት ሙከራ በባህር ዳር ከተማ በኩል እንዲሁም ብርሀኑ በቀለ አሻምቷት ብሌስ ናጎ በግንባር ያደረጋት ሙከራ ደግሞ በሲዳማ ቡና በኩል የተደረጉ የአጋማሹ መጀመሪያ ሙከራዎች ሲሆኑ በ61ኛው ደቂቃም ሲዳማ ቡናዎች መሪ ያደረጋቸውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። መስፍን ታፈሰ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ አክርሮ በመምታት ያስቆጠራት ድንቅ ግብም ሲዳማ ቡናዎችን መሪ ያደረገች ግብ ነች።
ግብ ካስተናገዱ በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት አጥቅተው በመጫወት በሄኖክ ይበልጣል እና በፍፁም ፍትሐአለው አማካኝነት ሙከራዎች ያደረጉት ባህርዳር ከተማዎች በ71ኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ሰቲህ ኦሴይ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች በአግባቡ ያላራቁትን ኳስ ተጠቅሞ በደረቱ አብርዶ ከመረብ ጋር ባዋሀደው ኳስ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
ከግቦቹ መቆጠር በኋላ የጣና ሞገዶቹ በሰቲህ ኦሴ አማካኝነት ባደረጓቸው ሁለት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች፤ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ያሬድ ባየህ ባልተጠቀመበት ዕድል ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት 1 ለ 1 በሆነው ውጤት ተጠናቋል።

