ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ሲጋሩ ነገሌ አርሲዎች ወሳኝ ድል አሳክተዋል

ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ሲጋሩ ነገሌ አርሲዎች ወሳኝ ድል አሳክተዋል

ምዓም አናብስት እና ቡናማዎቹ ያፋለመው ጨዋታ 1-1 ሲጠናቀቅ ሰጎኖቹ ከመሪው ያላቸውን ልዩነት ያጠበቡበትን ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል

 

 

መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮጵያ ቡና

 

በዕለቱ መርሐ ግብር መቐለ 70 እንደርታን ከ ኢትዮጵያ ቡና ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያውን አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ኢትዮጵያ የተሻለ ቢሆንም ግቦችን ለማግኘት ግን ሁለቱም ቡድኖች በከፍተኛ ተነሳሽነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የግብ አደጋዎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። ግብ በማስቆጠር ረገድ ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀዳሚ የነበሩ ሲሆን 19ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ራምኬል ጀምስ በግንባሩ በመግጨት የውድድር ዘመኑን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

ነገር ግን መሪነታቸው መዝለቅ የቻለው ለጥቂት ደቂቃ ብቻ ነበር። 31ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ አለማየሁ እና ግብጠባቂው ታምራት በተፈጠረ አለመግባባት በፍቃዱ አለማየሁ በራሱ ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ አቻነት መልሷል። አጋማሹ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ታምራት ቅባቱ የመለሰው ሲሆን አሸናፊ ሀፍቱ የተመለሰውን ኳስ በድጋሚ ቢመታውም በግብ ጠባቂው ተጋድሎ ግብ ከመሆን ድኗል።

ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን 20 ያክል ደቂቃዎች ቡናማዎቹ ብልጫን መውሰድ የቻሉ ቢሆንም በተቀሩትን ደቂቃዎች ጫናዎችን ፈጥረው ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ግን ምዓም አናብስት ነበሩ። ይህንንም ተከትሎ ፍፁም አለሙ 74 ኛው ደቂቃ ላይ ሳጥን ውስጥ ሞክሮ ግብ ጠባቂው በመለሰበት እንዲሁም 76ኛው ደቂቃ ላይ የግቡን አግዳሚ በገጨበት ወርቃማ ዕድሎች መሪ የሚሆኑበት ግብ ለማግኘት ቢቃረቡም ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቶ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

 

 

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ነጌሌ አርሲ

 

ሁለቱም ቡድኖች ተቀራራቢ የሆነ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የወሰዱበት የመጀመሪያው አጋማሽ በፈጣን ሽግግሮች እና በሙከራዎች የታጀበ ነበር። ፈጣን የሆኑ የመስመር አጥቂዎቻቸውን ኢላማ ባደረጉ ፈጣን ሽግግሮች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሰጎኖቹ ሮኅቦት ሰላሎ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት በመታው እና ነጥሮ በግብ ጠባቂው ጥረት በግቡ አናት ከወጣው ሙከራ በኋላ 23ኛው ደቂቃ ላይ ከቤ ብዙነህ ከቅጣት ምት በቀጥታ ባስቆጠረው ድንቅ ግብ መሪ መሆን ችለዋል። በአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ዘሩባቤል ፈለቀ ከሳጥን ውጭ ያደረጋት እና ግብ ጠባቂው አማኑኤል ደስታ በጥሩ ቅልጥፍና ግብ ከመሆን የታደጋት ሙከራም የሰጎኖቹን መሪነት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።

ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ከደቂቃዎች በኋላ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ተከላካይ ዮናስ ለገሰ ከቤ ብዙነህ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተ ሲሆን ሰጎኖቹም የቁጥር ብልጫውን ተጠቅመው ጫናዎችን መፍጠር ችለዋል። 64ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሳጥን ውስጥ ዳዊት ተፈራ ላይ ጥፋት መሰራቱን ተከትሎ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ዳዊት ተፈራ ወደ ግብነት ቀይሮ የግቡን ልዩነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ንግድ ባንኮች ጫናዎችን ፈጥረው መጫወት ቢችሉም የነጌሌ አርሲን የመከላከል አደረጃጀት ማለፍ ተስኗቸው ጨዋታው በነጌሌ አርሲ 2 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።