ሪፖርት | ዋልያዎቹ በመልስ ጨዋታ ሳኦቶሜን በመርታት ወደ ምድብ ማጣሪያው ተቀላቅለዋል

ሪፖርት | ዋልያዎቹ በመልስ ጨዋታ ሳኦቶሜን በመርታት ወደ ምድብ ማጣሪያው ተቀላቅለዋል

ዋልያዎቹ በድሬዳዋ ስታዲየም ባደረጉት የመልስ ጨዋታ የሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ አቻቸውን 1 ለ 0 በማሸነፍ፣ በድምር ውጤት 4 ለ 0 በመርታት ወደ ምድብ ማጣሪያ ተሸጋግረዋል።

በድሬዳዋ ስታዲያም ደጋፊዎቻቸው ፊት የቀረቡት ዋሊያዎቹ ከጨዋታው ጅማሮ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን በመውሰድ ተጋጣሚያቸውን መጫን ጀምረዋል። በዚህም ጨዋታ ገና ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቀዳሚ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። መስፍን ታፈሰ ተከላካዮችን በቀላሉ አታሎ በማለፍ ያለቀ ኳስ ወደ ሳጥን መሬት ለመሬት አሻግሯት ብቻውን ሆኖ ተመቻችቶ ሲጠባብቅ የነበረው ቸርነት ጉግሳ በግሩም ሁኔታ መረብ ላይ አሳርፎ ዋልያዎቹን መሪ አደርጓቸዋል።

ወደ ጨዋታ ለመመለስ ወደ ፊት መምጣት የጀመሩት ሳኦቶሜዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በመስመር በኩል ገብተው በጠባብ አንግል ወደ ግብ የመቱትን አደገኛ ኳስ የዋሊያዎቹ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ እንዴትም ባያግድባቸው አቻ ለመሆን ቀርበው የነበሩበት የተሻለው ሙከራ ነበር። 25ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው በቆመ ኳስ ያደረገው ሙከራም ኢላማውን ሳይጠብቀለት ቀርቷል፤ እንዲሁም ቸርነት ጉግሳ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ዞሮ መጥቶ ግብ ጠባቂው እንዴትም ባይመልስባቸው ዋሊያዎቹ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት የቀረቡበት አጋጣሚ ነበር።

እስከ መጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ድረስ ዋሊያዎቹ ሙሉ በሙሉ ብልጫ በመውሰድ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ግብ ላይ በመድረስ ረገድ የበላይ የነበሩበት ቢሆንም፣ ተጫማሪ ግብ ለማግኘት የተፈጠሩት ወርቃማ የግብ እድሎች ግን ወደ ግብነት ሳይቀይሩ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ የታየው  እንቅስቃሴ ከመጀመሪያው አጋማሽ በበለጠ ብርቱ ፉክክር የታየበት እና በሙከራዎች የታጀበ ነበር። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ የኳስ ቁጥጥር ብልጫውን በመውሰድ ተጋጣሚያቸውን በራሱ ሜዳ ተገድቦ እንዲከላከልም አስገድደውታል።

​ዋሊያዎቹ በሁለቱም የመስመር አጥቂዎቻቸው በኩል ወደ ሳጥን የሚላኩ ኳሶችን በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ 60ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል ሳጥን ውስጥ ደርሶ መስፍን ታፈሰ ከመስመር በኩል አሻግሮ ሳይጠቀሙበት የቀሩት አስቆጪው አጋጣሚም ይጠቀሳል። በአንፃሩ ሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔዎች ሙሉ በሙሉ በመከላከል ላይ ተመስርተው አልፎ አልፎ በሚገኙ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል ለመድረስ ቢሞክሩም የዋሊያዎቹ ተከላካዮች ግን በንቃት አክሽፈውባቸዋል። በተለይም 65ኛው እና 66ኛ ደቂቃ ላይ ያደረጉት ሁለት ሙከራዎች ሲጠቀሱ ከሳጥን ውጪ ሆነው ያደረጉት ሁለቱም አጋጣሚዎች ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ ከፍ ብሎ አልፎባቸዋል። እንዲሁም በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቀይረው ካሰገቡ በኋላ የተነቃቁት ሳኦቶሚዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ ሌላኛውን አደገኛ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው እንዴትም አድግዶባቸዋል።

በአጠቃላይ በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን ተመጣጣኝ በሚባል ደረጃ መከናወን የቻለ ሲሆን ምንም እንኳን የተፈጠሩት በርካታ የግብ እድሎች ወደ ግብ ባይቀየሩም በቡድኖቹ እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ የነበረው የማጥቃት ፍላጎት በስታዲያሙ ለነበሩ ደጋፊዎች የሚስብ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል። የመልሱ ጨዋታም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 1ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቆ በድምር ውጤት 4ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የምድብ ድልድል መቀላቀሉን አረጋገጧል።