ሰጎኖቹ የዓመቱ የመጀመሪያ ድል አስመዘገቡ

ሰጎኖቹ የዓመቱ የመጀመሪያ ድል አስመዘገቡ

በአብዩ አረጋሽ

ነጌሌ አርሲዎች በውድድር ዓመቱ በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ግብ በላይ ግብ በማስቆጠር ኢትዮጵያ ቡናን ረቱ

በአዲስ አበባ ስታድየም ቀን 9፡00 ሰዓት በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመድረስ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችሎ ነበር። ሆኖም የፈጠራቸውን ዕድሎች ወደ ግብነት መቀየር ባለመቻሉ ቀድሞ መሪ የመሆን ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ነገሌ አርሲ በበኩሉ የተጋጣሚውን ስህተቶች በመጠቀም የግብ ዕድሎቹን በብቃት ወደ ግብነት መቀየር ችሏል። በ20ኛው ደቂቃ ራምኬል የፈጠረውን ስህተት ተከትሎ ከከቤ ብዙነህ የተላከለትን ኳስ ገብረመስቀል ዱባለ ወደ ግብነት በመቀየር ሰጎኖቹን መሪ አድርጓል።

የመጀመሪያዋን ግብ ካስቆጠረ ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ በ28ኛው ደቂቃ ነገሌ አርሲ በድጋሚ የግብ ዕድል አግኝቷል። በፍጹም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ራምኬል በገብረመስቀል ዱባለ ላይ በፈጸመው ጥፋት የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ ወደ ግብነት በመቀየር የነገሌ አርሲን መሪነት ወደ 2 ከፍ አድርጓል።

በቀሩት የአጋማሹ ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡና ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም ነገሌ አርሲዎች መሪነታቸው አስጠብቀው የመጀመሪያውን አጋማሽ በ 2 ለ 0 መሪነት አጠናቀዋል።

ከዕረፍት መልስ ኢትዮጵያ ቡና የተሻለ አጀማመር በማድረግ የኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለማስጠበቅ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። የቡና ተጫዋቾች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ ጨዋታውን ለመቀየር ቢሞክሩም የፈጠሯቸውን ዕድሎች ወደ ግብነት መቀየር አልቻሉም።

ነገሌ አርሲም በበኩሉ በተገኙት ዕድሎች የተጋጣሚውን የግብ ክልል በመፈተሽ የግብ ሙከራዎችን ማድረጉን ቀጥሏል። ጨዋታው ወደ መጨረሻው ደቂቃዎች ሲደርስም የነገሌ አርሲ የበላይነት በውጤቱ ላይ ተጠብቆ ቆይቷል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለመጠናቀቅ ሲቃረብም ድልአዲስ ገብሬ በተስፋዬ በቀለ ላይ በፈጸመው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። በዚሁ ጥፋት ምክንያት ለነገሌ አርሲ የተሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት ኮሊን ኮፊ በብቃት ወደ ግብነት በመቀየር የቡድኑን መሪነት ወደ 3 ከፍ ማድረግ ችሏል። በዚህም ነገሌ አርሲ በገብረመስቀል ዱባለ፣ በዳዊት ተፈራ እና በኮሊን ኮፊ ግቦች ኢትዮጵያ ቡናን 3 ለ 0 በመርታት የሦስተኛ ሳምንቱን የሊግ ጨዋታ በድል አጠናቋል።