ኮንፌድሬሽንስ ዋንጫ ፡ ‹‹ ጨዋታውን አሸንፈን እንደምንመለስ አምናለሁ ›› ጋብሬል አህመድ

የ2006 የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው ደደቢት በ2015 የአፍሪካ ኮንፌድሬሽንስ ዋንጫ የመጀመርያ ጨዋታ ከሲሸልሱ ኮት ዲ ኦር ጋር ይጫወታል፡፡ ቅዳሜ ለሚያደርገው ጨዋታም ዛሬ አመሻሽ 11፡00 ላይ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በኬንያ በኩል ሐሙስ ወደ ስፍራው እንደሚደርስ ታውቋል፡፡

የሲሸልሱ ተጋጣሚ ኮት ዲ ኦር 2,000 ተመልካች የሚይዝ ስታድ አሚቴ የተሰኘ የራሱ ሜዳ ያለው ሲሆን ከዋና ከተማው ቪክቶርያ የ15 ደቂቃ በረራ ርቀት ላይ በምትገኘው ፔርስሊን ደሴት ይገኛል፡፡

ስለ ጨዋታው ሶከር ኢትዮጵያ ያነጋገረቻቸው የደደቢት አምበል ብርሃኑ ቦጋለ እና አማካዩ ጋብሬል አህመድ ለጨዋታው እንደተዘጋጁና አሸንፈው እንደሚመለሱ ተናግረዋል፡፡

Birhanu

‹‹ የቡድናችን መንፈስ ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የሊግ ጨዋታ እና የአፍሪካ ውድድር የተለያየ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሰጥተን ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ›› ሲል ብርሃኑ ቦጋለ አስተያየቱን የሰጠ ሲሆን አያይዞም ከጉዳቱ እያገገመ መሆኑንም ተናግሯል፡፡

‹‹ ከሀዋሳው ጨዋታ ጉዳት እያገገምኩ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም 80 በመቶ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆንኩ ይሰማኛል ››

ጋናዊው አማካይ ጋብሬል አህመድ በበኩሉ ጥሩ ዝግጅት እንዳደረጉና ከሜዳ ውጪ አሸንፈው እንደሚመለሱ ያለውን እምነት ገልጧል፡፡

‹‹ ጥሩ አሰልጣኝ አለን፡፡ ደስተኛ ሆነን እየሰራን ነው፡፡ ስለ ተጋጣሚያችን ብዙም ባናውቅም እኔ በግሌ ዩ ቲዩብ ላይ ለመመልከት ሞክሬያለው፡፡ የአጨዋወት ስታይላቸው እና ተጫዋቾቻቸውን ተመልክቻለሁ፡፡ እንደማስበው እዛ አሸንፈን የመምጣት እድል አለን፡፡ ጨዋታውን ጨርሰን እንደምንመለስም እርግጠኛ ነኝ፡፡ አሁን በቡድኑ ውስጥ የወጣቶች እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ስብጥር ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ ጉልበት ፤ ልምድ እና ክህሎት ከጥሩ አሰልጣኝ ጋር አጣምረን በመያዛችን ጥሩ ጉዞ እናደርጋለን ብለን እናስባለን፡፡ ››

በተያያዘ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቡድኑን የተቀላቀለው ያሬድ ዝናቡ ከደረሰበት ጉዳት እያገገመ መሆኑን ተነግሯል፡፡ ‹‹ ከሲቲ ካፑ በኋላ በጉዳት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ርቄያለው፡፡ አሁን ግን በሙሉ ጤንነት ላይ እገኛለው፡፡ ከኮት ዲ ኦር ጋር ለምናደርገው የመልስ ጨዋታ እንደምደርስ ተስፋ አደርጋለሁ ›› ብሏል፡፡

ደደቢት ቅዳሜ በእኛ ሰአት አቆጣጠር በ9 ሰአት ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *