-
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከእሁዱ የሌሴቶ ድል በኋላ ፊቱን ከኬንያ ጋር ወደሚጠብቀው የቻን ማጣርያ ጨዋታ አዙሯል፡፡ ቡድኑ በትናንትናው እለት 10፡00 ላይ ልምምዱን የሰራ ሲሆን የልምምድ ፕሮግራሙ በአመዛኙ በሌሴቶው ጨዋታ ላይ ባልተሳተፉት ተጫዋቾች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረው ኤፍሬም አሻሞም ልምምድ ሰርቷል፡፡
በልምምዱ የአካል ብቃት ስራዎች ከፍተኛውን ሰአት የወሰዱ ሲሆን ጠንከር ያሉ የአካል ብቃት ልምምዶች ሲሰሩ ተስተውሏል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ተጨዋቾችን ጥንድ ጥንድ በማድረግ የመከላከል እና አልፎ ግብ የማስቆጠር ልምምዶችን ሲሰሩ 50/50 ኳሶችን የማሸነፍ ፣ በጠባብ ቦታዎች ተጫዋቾችን የማለፍ ቴክኒኮች የልምምዱ አካል ነበሩ፡፡
ከትናንቱ ልምምድ በመነሳት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የቻን ቡድናቸውን በሌሴቶው ጨዋታ ከተጠቀሙባቸው ተጫዋቾች ውጪ ባሉት ተጨዋቾች ቡድናቸውን ሊያዋቅሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለ2016 የቻን ውድድር ለማለፍ የሚያከናውኑት የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታ በመጪው እሁድ የሚካሄድ ቢሆንም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ውድድሩ የሚካሄድበትን ስፍራ አስካሁን በይፋ አላስታወቀም፡፡