“ሳላ ወደ አልጄሪያ እየሄደ አይደለም” አብዱልራህማን መግዲ

የኢትዮጵያዊው አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ ወኪል የሆኑት ግብፃዊው አብዱልራህማን መግዲ ሳላዲን ወደ አልጄሪያው ክለብ ኤምሲ አልጀርስ ሊያቀና ነው የሚሉትን ዜናዎች ከእውነት የራቀ በማለት አጣጥለዋል፡፡ አብዱልራህማን መግዲ ስለተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት “ሳላ ወደ አልጄሪያ እየሄደ አይደለም፡፡ በአሁን ሰዓት ስለዝውውሩ ማውራት አልችልም፡፡ ስለዝውውሩ የተነሳው ዘገባ ከእውነት የራቀ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

በግብፁ አል አሃሊ ኑሮ የከበደው የሚመስለው ሳላዲን ክለቡ በመጪው የዝውውር መስኮት ሊለቀው እንደሚችል ከግብፅ የሚመጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የምዕተ ዓመቱ የአፍሪካ ምርጥ ክለብ አል አሃሊ ባሳለፍነው ሳምንት ጋናዊውን የቀድሞ የኢስማኤሊ አጥቂ ጆን አንትዊን ከሳዑዲ አረቢያው ክለብ አል ሻባብ በ1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማስፈረሙ የሳላዲንን በክለቡ የሚኖረውን ቆይታ አጣራጣሪ አድርጓታል፡፡ ስለጉዳዩ አብዱልራህማ መግዲ “ስለአል አሃሊ የወደፊት ቆይታው አሁን ላይ መናገር ያስቸግራል፡፡” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አብዱልራህማን መግዲ የኢትዮጵያዊያኖቹ ሳላዲን ሰዒድ እና ሽመልስ በቀለ ወኪል ናቸው፡፡ ሳላዲን ሰዒድ ለአል አሃሊ 4 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡