ሳላዲን ለኤምሲ አልጀርስ ሊፈርም ተቃርቧል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አምበል ሳላዲን ሰኢድ ወደ አልጄርያው ኤምሲ አልጀርስ የሚያደርገው ዝውውር ከጫፍ መድረሱን ከአልጄርያ የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የኤምሲ አልጀርሱ ፕሬዝዳንት አብዱልከሪም ሬሲ ለኤፒኤስ በሰጡት አስተያየት ሳላዲን ለማዘዋወር የሚፈልጉት አይነት ተጨዋች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ ሳለዲን ምርጥ ተጫዋች ነው፡፡ እርሱ እኛ እንዲጫወትልን የምንፈልገው አይነት አጥቂ ነው፡፡ ተጫዋቹ ከኤምሲ አልጀርስ ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ በዚህ ሳምንት አልጀርስ መገኘት አለበት፡፡ ›› ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ሳላዲን ሰኢድ ባለፈው ሳምንት ብሄራዊ ቡድኑ ሌሶቶን 2-1 ሲያሸንፍ ማሸነፍያዋን ግብ ከመረብ በማሳረፍ የብሄራዊ ቡድኑ ሁነኛ ሰው መሆኑን ቢያስመሰክርም በግብፁ አል-አህሊ ህይወት ከብዶታል፡፡ በጉዳት እና በተጠባባቂ ወንበር በመቀመጥ በአፍሪካውን ታላቅ ክለብ ይህ ነው የሚባል ታሪክ መስራት ተስኖታል፡፡

እንደ ፕሬዝዳንቱ አስተያየት ሳላዲን ከክለቡ ጋር ከስምምነት ላይ የሚደርስ ከሆነ በጁላይ ወር ክለቡ ከቤሎዊዝዳድ ጋር በሚያደርገው የ2015/16 የውድድር ዘመን መክፈቻ የደርቢ ፍልሚያ ላይ ይሳተፋል፡፡