​አፈወርቅ ዮሀንስ – 24 የውድድር ዘመን በተጫዋችነት. . .

በኢትዮዽያ የእግርኳስ ተጫዋቾች በሊግ ደረጃ ያላቸው የጨዋታ እድሜ እምብዛም ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶችም ብዙ የውድድር ዘመን ሳያሳልፉ ከእግርኳስ አለም የሚገለሉ ተጫዋቾች በርካታ ናቸው፡፡ ቡታጅራ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረከተውና በሊጉ የተለያዩ እርከኖች በሚገኙ ክለቦች ያሳለፈው አፈወርቅ ዮሀንስ ግን በአስገራሚ ሁኔታ ለ25ኛ የውድድር ዘመኑ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡

በመልካም ባህርዩ በርካቶች የተከበረው አፈወርቅ ዮሐንስ የእግር ኳስ ህይወቱን ሀ ብሎ የጀመረው በትምህርት ቤት ውድድር በአርባምንጭ ከተማ ላይ ሲሆን በክለብም ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ የተጫወተው አርባምንጭ ውስጥ ለነበረ እርሻ ጣቢያ ክለብ በመጫወት ነው። ከዛ በመቀጠል ለክልል ሻምፒዮና ባሳየው ብቃት በ1986 ወደ ሀዋሳ ከተማ በመምጣት ለአምስት አመት የተሳካ ቆይታ አድርጓል፡፡ በመቀጠል በሌሎች የፕሪምየር ሊግ ክለቦች በነበሩት ትራንስ ኢትዮዽያ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዳማ ከተማ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ በብሔራዊ ሊግ (በወቅቱ 2ኛ እርከን ላይ ይገኝ ነበር) ሜታ ቢራ ፣ ሼር ኢትዮዽያ ፣ ሻሸመኔ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ የተጫወተው አፈወሮቅ አምና በከፍተኛ ሊጉ ለሰሜንሸዋ ደብረብርሀን ተጫውቷል፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ደግሞ የብሔራዊ ሊጉ ‘ምድብ ሠ’ን በቀዳሚነት አጠናቆ ወደ ከፍተኛ ሊግ ባደገው ቡታጅራ ከተማ ይገኛል፡፡

የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ አፈወርቅ ስላሳለፈው ረጅም የአግርኳስ ህይወት ሰለከር ኢትዮጵያ እንዲህ ባለ መልኩ አስተያየቱነ ሰጥቷል፡፡ ” እስካሁን ባለው የእግር ኳስ ህይወቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ይህን ያህል አመት የመጫወቴ ምክንያት የፈጣሪ ስጦታ ነው፡፡ አሁን ካሉት ወጣቶች በፍጥነትም ሆነ በጉልበት ተሽዬ ሳይሆን የውስጥ ጥንካሬ ነው ለረጅም አመት እንድጫወት የረዳኝ። ሌላው  አሰልጣኞች በሚሰጡት ልምምዶች ሁሉ በቂ ዝግጅት አደርጋለው ” ይላል፡፡

ለሩብ ምዕተ አመት በተጠጋው የተጫዋችነት ህይወቱ ከተለያዩ የእግርኳስ ትውልዶች ጋር ያሳለፈው በምርጥ አቋሙ የነበረበትን ጊዜ ከአሁኑ ጋር ያነፃጽራል፡፡ “ብዙ የተለየ ነገር የለም፡፡ ካለም አሁን በአሰልጣኞች  የሚሰጠው የአሰለጣጠን መንገድ ዘመናዊ መሆኑ እንጂ መሰረታዊ የሆነ ልዩነት የለም። ከዚህ ባሻገር ደግሞ በዚህ ዘመን በሚገኙ ተጨዋቾች ላይ ዘላቂና ወጥ የሆነ ነገር አትመለከትም፡፡ ሌላው እኔ በግሌ በቅርብ ያየሁት ለውጥ ብሔራዊ ቡድኑ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመራ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መግባታችን ነው  እንጂ እስካሁን ያየሁት ብዙ ለውጥ የለም። ሆኖም በእግር ኳሳችን ላይ ብዙ ስራ መሰራት ይጠበቅብናል፡፡ በእኛ ዘመን በተጨዋቾቹ በኩል ተመሳሳይ የሆነ አቅም ስለነበር ለመሰለፍ ካለህ ጉጉት የተነሳ ጠንክራ ስራ ይጠብቅሀል ”

በቀጣይ አመት በሊግ ደረጃ መጫወት ከጀመረ 25 አመት የሚሞላው አፈወርቅ በቀጣይም መጫወት እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡ ” በቀጣይ በከፍተኛው ሊግ ከቡታጅራ ጋር አብሬ እቆያለው፡፡ ከዛ በኋላ ግን ለቤተሰቤ እንዲሁም ለአንዳንድ ላሰብኳቸው ነገሮች ሲባል በ2010 መጨረሻ ላይ ጫማዬን እሰቅላለው ብዬ አስባለው። እግር ኳስን ካቆምኩ በኋላ ወደ አሰልጣኝነቱ ጎራ የመቀላቀል ፍላጎት አለኝ፡፡ አሁን የ C ላይሰንስ ወስጃለው ፤  በቀጣይ አመት ሁለተኛ ደረጃ የB ላይሰንስ ስልጠና በመውሰድ እግር ኳስ ሳቆም ወደ አሰልጣኝነቱ ለመመለስ አስቤያለሁ” ሲል አስተያየቱን አጠቃሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *