19 አሰልጣኞች ወደ በሞሮኮ የአሰልጣኞች ስልጠና መውሰድ ጀመሩ

የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሞሮኮ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ በመተባበር የተዘጋጀው የአሰልጣኞች ስልጠና ከነሐሴ 30 እስከ መስከረም 6 ቀን ይካሄዳል፡፡ አሰልጣኞቹም ወደ ሰፍራው አምርተው ስልጠናውን መከታተል ጀምረዋል፡፡

አሰልጣኞቻችን በስልጠናው ላይ በሚኖራቸው ቆይታ አሁን አለም ከደረሰበት ዘመናዊ እግር ኳስ የስልጠና ዘዴ ጋር እንዲተዋወቁ እና ልምድ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሎለታል። በዚህ ስልጠና አስቀድሞ እንዲሳተፉ ለሠላሳ ሰልጣኞች እድሉ እንደተመቻቸ ቢነገርም ወደ ሞሮኮ ያቀኑት ግን 19 ሰልጣኞች ብቻ መሆኗቸው ታውቋል። በተለይ የዚህ እድል ተጠቃሚ የሆኑት የብሔራዊ ቡድን ፣ የፕሪምየር ሊግ ሴቶች እና ወንዶች እንዲሁም የከፍተኛ ሊግ አሰልጣኞች ናቸው ።

የአሰልጣኞች ስልጠናውን የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዕድሉን ያመቻች እንጂ የአሰልጣኞችን ሙሉ አስፈላጊ ወጪ በመሸፈን ድጋፍ ያደረጉት አሰልጣኞቹ የወከሏቸው ክለቦች እንደሆኑ ታውቋል።

በስልጠናው ለመካፈል የተጓዙት የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የዋልያዎቹ እና የሉሲ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እና መሰረት ማኒ ፤ ከፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች መካከል አለማየሁ አባይነህ ( ሲዳማ ቡና ) ፣ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ( ወልድያ ) ፣ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ( አርባምንጭ ከተማ ) ፣ ምንተስኖት ጌጡ ( ፋሲል ከተማ ) ፣ ብርሃኑ ባዩ (ኤሌክትሪክ) ፤ ከሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞች ሰላም ዘርአይ ( ቅዱስ ጊዮርጊስ ) ፣ ኢየሩሳሌም ነጋሽ ( ኢትዮዽያ ቡና ) ፣ ፍሬው ወ/ገብርኤል ( ሲዳማ ቡና ) ፣ ዮሴፍ ገብረወልድ ( ሀዋሳ ከተማ ) ፣ ብዙአየሁ ዋዳ ( ልደታ) ፣ ፍስሀ ጥዑመልሳን ( ድሬዳዋ ከተማ ) ፣ ዳዊት ( ቦሌ ) ከከፍተኛ ሊግ አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሀም ( አክሱም ከተማ ) ፣ አብዲ ( ቡራዮ ከተማ ) እና ሁለት ስማቸውን ማግኘት ያልቻልናቸው ተጨማሪ አሰልጣኞች ወደ ሞሮኮ ተጉዘዋል።

ለሁለት ተከፍሎ ቅዳሜ እና ሰኞ ያቀኑት አሰልጣኞቹ ሪቬ ሆቴል ማረፊያቸውን ያደረጉ ሲሆን ትላንት ማምሻውን አብረው ከአሰልጣኞቹ ጋር ያቀኑት የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደት አቶ ጁነዲን ባሻ በስልጠናቸው ወቅት ስለሚኖሯቸው ቆይታ እና ተያይዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙርያ ንግግር አድርገዋል፡፡ ሰልጣኞቹም ለፌዴሬሽኑ ይህን እድል በማመቻቸቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ስልጠናው በሀገሪቱ እውቅ ኢንስትራክተሮች ከዛሬ ከጀምሮ ለ15 ቀናት በንድፈ ሀሳብ እና በሜዳ ላይ የተግባር ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ የሞሮኮ የእግር ኳስ ማዕከላትን ፣ የእግር ኳስ መሰረተ ልማቶችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ።

እንደነዚህ ያሉ ስልጠናዎች መኖራቸው ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነው ሁሉ አሰልጣኞቻችን የሚያገኙትን እውቀትና ልምድ በሚገባ መሬት ላይ በማውረድ ሊሰሩበት ይገባል መልዕክታችን ነው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *