​ቅድመ ውድድር ዝግጅት – ወላይታ ድቻ

ለመጀመርያ ጊዜ በአፍሪካ ውድድር የሚሳተፈው ወላይታ ድቻ በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እየተመራ የውድድር አመት ዝግጅቱን በቦዲቲ እያደረገ ይገኛል።

ወደ ፕሪምየር ሊጉ ከተቀላከለበት ከ2006 ጀምሮ ከታችኛው ሊጎች በአነስተኛ የዝውውር ወጪ ተጨዋቾችን በማስፈረም ተፎካካሪ ቡድን  በመገንባት ለአብዛኛዎቹ የፕሪምየር ሊግ ቡድኖች ፈታኝ ሆኖ መዝለቅ የቻለው ወላይታ ድቻ በ2009 የፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ባልተለመደ ሁኔታ ከነበረው ጥንካሬ ተዳክሞ በቀላሉ ጎል የሚያስተናገድ እና ተገማች አቀራረብ ይዞ የሚገባ ቡድን ሆኖ ላለመውረድ ሲታገል ቆይቶ የመጨረሻውን ሳምንት ጨዋታ በማሸነፍ በሊጉ መሰንበቱን ማረጋገጡ ይታወሳል።

ወላይታ ድቻ በሊጉ ያሳየው አቋም ደካማ ቢሆንም ለክለቡ እንደ ትልቅ ድልና ስኬት የሚወሰደው በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ አሸናፊ በመሆን በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ መሆኑን ማረጋገጡ ነው።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በክለቡ ለተጨማሪ አመት እንዲቆዩ ማድረግ የቻለው ወላይታ ድቻ በዘንድሮ አመት በፕሪምየር ሊጉ እና በአፍሪካ መድረክ ለሚኖረው ተሳትፎ በማሰብ ያልተመዱ የዝውውር እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል። ከሀገር ውስጥ ተጨዋቾችን የታችኛው የሊግ እርከን በማስፈረም ከሚታወቅበት አሰራር በመውጣት በፕሪምየር ሊጉ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን በከፍተኛ ሂሳብ ከማምጣቱ ባሻገር በክለቡ ታሪክ የመጀመርያውን የውጭ ተጨዋቾችን ማስፈረም ችሏል።

ወላይታ ድቻ ባሳለፍነው የውድድር አመት በ30 ጨዋታ 9 ሲያሸንፍ 12 ተሸንፎ 9 ጨዋታን በአቻ ውጤት አጠናቆ 30 ጎል ሲቆጠርበት 24 ጎል አስቆጥሮ 36 ነጥብ በመያዝ በደረጃ ሰንጠረዡ 9ኛ በመሆን አጠናቋል።

ከወላይታ ድቻ ጋር የተለያዩ ተጨዋቾች ግብ ጠባቂው ወንደሰን አሸናፊ ፣ ተከላካዮቹ ቶማስ ስምረቱ ፣ ፈቱዲን ጀማል ፣ ዳግም ንጉሴ እና  አናጋው ባደግ ፣ አማካዮቹ አማኑኤል እሸቱ እና ዮሴፍ ደንገቶ እንዲሁም አጥቂዎቹ እንዳለ መለዮ እና አላዛር ፋሲካ ናቸው።

አዲስ ፈራሚዎች

ለአዲሱ የውድድር አመት በወላይታ ድቻ መለያ የምንመለከታቸው ከፕሪሚየር ሊግ ቡድኖች ክለቡን የተቀላቀሉት ተጫዋቾች ተስፉ ኤልያስ ( ተከላካይ/ ሀዋሳ ከተማ) ፣ እሸቱ መና( ተከላካይ/አዳማ ከተማ)  ፣ አሳልፈው መኮንን ( ተከላካይ / ኢትዮ ኤሌክትሪክ) ፣ ኃይማኖት ወርቁ ( አማካይ/ሀዋሳከነማ) ሲሆኑ ከከፍተኛ ሊግ ክለቦች እርቅይሁን ተስፋዬ ( ተከላካይ/ሀድያ ሆሳዕና) ፣ አምረላህ ደልታታ ( አማካይ/ሀድያ ሆሳዕና) ወላይታ ድቻን የተቀላቀሉ ተጨዋቾች ናቸው።

ጃኮ አራፋት

ከሀገር ውጭ ወላይታ ድቻን በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የክለቡን ማልያ የሚለብሱ የውጭ ተጨዋቾች በመሆን ስማቸውን ማስመዝገብ የቻሉት ኢማኑኤል ፌቮ (ግብጠባቂ/ንግድ ባንክ) እና ጃኮ አራፋት (አጥቂ/ሀዋሳ ከተማ) ናቸው ።

አሁን ያለውን ስብስብ ለማጠናከር እና ጠንካራ ቡድን ለመስራት ከክለቡ ባገኘነው መረጃ መሰረት በቅርብ ቀናት ከቻድ እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተጨማሪ ሦስት ተጨዋቾች ከቡድኑ ጋር ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ አረጋግጠናል።

ከተስፋ ቡድን በሙከራ ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች

ከ17 እና ከ20 አመት በታች  ቡድን ወደ ዋናው ቡድን ለማሳደግ ለስምንት ታዳጊዎች የሙከራ እድል እየሰጠ ሲሆን እነሱም  እዮብ አየለ ፣ በለጠ ዘውዴ ፣ ታደለ ዳልጋ ፣ ውብሸት ክፍሌ ፣ ቸርነት ጉግሳ ፣ ምስክር መለሰ ፣ ብሩክ በለጠ ፣ ቢንያም ገነቱ ናቸው፡፡

ዝግጅቱን ዋናው የሶዶ ስታድየም ሜዳ በእድሳት ላይ በመሆኑ ምክንያት ሶዶ በሚገኘው የክለቡ ካምፕ ማረፊያውን አድርጎ ወደ ቦዲቲ ከተማ ሜዳ በማቅናት በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን እየሰራ ሲሆን አዲሱ የክለቡ ፈራሚ ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ፌቮን ጨምሮ ወንድወሰን ገረመው ፣ አብዱልሰመድ አሊ እና አምበሉ ተክሉ ታፈሰ በጉዳት እና በሌሎች ምክንያት ከክሉቡ ጋር ዝግጅት እያደረጉ የማይገኙ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት የቡድኑ አባላት በሙሉ ዝግጅታቸውን በአግባቡ እየሰሩ እንደሆነ መመልከት ችለናል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዝግጅታቸውንና ክለቡ በአፍሪካ መድረክ ተሳታፊ እንደመሆኑ እያደረገ ስላለው ቅድመ ዝግጅት የሰጡንን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል

” ዝግጅታችንን በተለያየ መልኩ ነው የሰራነው፡፡ አንደኛ ቡድኑን በማጠናከር በወጡት ተጨዋቾች ምትክ ሌሎች አዳዲስ ተጨዋቾችን ከሀገር ውስጥም ከውጪ በማምጣት ላይ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ከታችኛው ቡድንም ታዳጊዎችን ከቡድኑ ጋር ቀላቅለናል፡፡  ዝግጅታችንን በአካል ብቃት ፣ ተጨዋቾቹን የማቀናጀት ፣ ከተስፋ ቡድኑ ጋር ጨዋታዎችን በማድረግ እና በመሳሰሉት መልኩ እየሰራን ጥሩ ነገሮች እያየን ነው። የበለጠ ደግሞ ወደ ውድድር ስንገባ የምናየው ጉዳይ ነው የሚሆነው። ፕሪምየር ሊጉ የሚራዘም ከሆነ ደግሞ የበለጠ ቡድኑን ለማቀናጀት ይረዳናል ብለን እናስባለን። በተረፈ በኮፌዴሬሽን ካፕ ሀገር ወክለን ነው የምንወዳደረው፡፡ የተሻለ ነገር ለመስራት ፍላጎቱ አለን ፤ ፍላጎትም ብቻ አይደለም ጥረቱም ይኖራል ፣ ብቃቱም ይኖራል፡፡ ከደጋፊዎቻችን ጋር በመሆን አንድ ነገር እናደርጋለን። በፕሪምየር ሊጉ ያለን የመከላከል ጥንካሬ ላይ ትንሽ ነገር ጨምረን በሀገር ደረጃ የተሻለ ነገር ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን፡፡”

ወላይታ ድቻ ራሱን የሚገመግምበት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሁሌም በሚሳተፍበት የደቡብ ካስትል ካፕ ከመስከረም 13 ጀምሮ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *