​ካፍ የኬንያን የቻን 2018 አዘጋጅነት መብት ነጥቋል

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) በጥር 2018 የሚስተናገደውን የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) የአዘጋጅነት መብትን ከኬንያ ላይ መንጠቁ ታውቋል፡፡ ኬንያ ውድድሩን ለማስተናገድ ያልተሳካ ጥረት ማድረጓን ተከትሎ የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጋና ርዕሰ መዲና አክራ ባደረገው ስብሰባ የምስራቅ አፍሪካዋ ሃገር ውድድሩን እንዳታዘጋጅ ወስኗል፡፡

ኬንያ በ2018 ውድድሩን ለማስተናገድ ተመርጣ የነበረ ቢሆንም ውድድሩን ለማስተናገድ የሚያስፈጉ ስታዲየሞች ጥገና ግን እስካሁን ድረስ ማለቅ አለመቻላቸው የቻን ዋንጫን እንዳታዘጋጅ አግዷታል፡፡ ከወር በፊት የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሃገሪቱ በቅርብ የተደረገው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉት ኡሁሩ ኬንያታ ተቀናቃኛቸውን ራይላ ኦዲንጋን በልጠው አሸንፈዋል ያለውን የኬንያ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሽሬ ዳግም አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑ መንግስት ፊቱን ወደ ምርጫው እንዲያዟር አድርጓታል፡፡ ይህንን ተከትሎም መንግስት ለቻን ውድድር መስተንግዶ የሰጠው ትኩረት የላላ ሁኗል፡፡ ኬንያ ውድድሩን በናይሮቢ፣ ማቻኮስ እና ሞምባሳ በሚገኙ አምስት ስታዲየሞች ለማስተናገድ አቅዳ የነበረ ሲሆን ከአምስቱ ስታዲየሞች ሁለቱ ብቻ በተሻለ ይዞታ ላይ ይገኛሉ፡፡

ካፍ ውድድሩን በኬንያ ፋንታ እንዲያዘጋጅ የመረጠው ሃገር አሁን ላይ ባየታወቅም ከሞሮኮ፣ ዛምቢያ እና ደቡብ አፍሪካ አንዱ ውድድሩን የማስተናገድ መብት ሊሰጠው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ ከ21 ዓመታት በፊት ኬንያ የ1996ቱን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ የነበረች ቢሆንም ልክ እንደአሁኑ ዝግጅት ላይ ደክመት ማሳየቷን ተከትሎ እድሉ ለደቡብ አፍሪካ ተሰጥቷል፡፡

በተያያዘ የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫን በ2019 እንድታስተናግድ ግብፅን መርጧል፡፡ ውድድሩ ለ2020 ቶኪዮ ኦሎምፒክ አፍሪካን ወክለው የሚወዳደሩ ሃገራትን የሚለይ ሲሆን ውድድሩን የማስተናገድ መብት የነበራት ዛምቢያ በእራሷ ፍቃድ ከማስተናገዱ እሯሷን ማግለሏ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *