የቤልጂየም እና ቱርክ ክለቦች ጋቶች ፓኖም ላይ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል

ጋቶች ፓኖም በቤልጂየም እና ቱርክ ክለቦች ዕይታ ውስጥ ገብቷል፡፡ ስማቸው ያልተጠቀሰው ክለቦቹ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እና የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ አማካይ ጋቶችን ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው ተብሏል፡፡
በቤልጂየም ሊግ የሚወዳደር አንድ ክለብ ፣ በቱርክ ሱፐር ሊግ እና የቱርክ ቲ.ኤፍ.ኤፍ አንደኛ ሊግ (አንደኛ ዲቪዚዮን) የሚወዳደሩ ሁለት ክለቦች ጋቶች ከሌሴቶ እና ኬንያ ጋር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ምስል የተመለከቱ ሲሆን ፤ ናይሮቢ ላይ በኬንያ እና ኢትዮጵያ መካከል በተደረገው የቻን የአፍሪካ ዋንጫ የመልስ ጨዋታ እኚህ ስማቸው ያልተጠቀሰው ክለቦች መልማዮቻቸውን ልከው ጋቶችን መገምገማቸውን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ በዋሊዎቹ ማሊያ መልካም እንቅስቃሴ ያሳየው ጋቶች ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቀሪ የ2 ዓመት ውል አለው፡፡ ይህም ክለቦቹን የዝውውር ጥያቄ ለኢትዮጵያ ቡና እንዳያቀርቡ እንቅፋት ኋኗል፡፡ ክለቦቹ በቀጣይ ግዜያት መልማዮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ ጋቶችን መመልከታቸው እንደሚቀጥሉ ተነግሯል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ጋቶችን የመሸጥ ምንም ዓይነት ፍለጎት የለውም፡፡ የቀጣይ ዓመት የቡና ዕቅድ ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብለው ከሚገመቱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡
ጋቶች በ2003 ዝዋይ ላይ በተደረገ የታዳጊዋች ውድድር ላይ የተመለከቱት አንጋፋው አሰልጣኝ ስዩም አባተ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ወስደውታል፡፡ በ2005 ለኢትዮጵያ ቡና በቋሚነት መሰለፍ የጀመረው ጋቶች በ2012 ዩጋንዳ ላይ በተደረገው የሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ካፕ ላይ ለብሄራዊ ቡድን መጫወት ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *