የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋዜጣዊ መግለጫ…

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ ረፋድ ላይ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጊዜያዊ ሰብሳቢ አቶ በለጠ ዘውዴ፣ አቃቢ ነዋይ ኢ/ር ኃይለየሱስ ፍስሀ እና ሌሎች የቢሮ ኃላፊዎች እንዲሁም የሚመለከታቸው የማህበር ማደራጀ አካላት በተገኙበት 5 ኪሎ በሚገኘው ወጣችና ስፖርት ቢሮ ነው ጋዜጣዊ መግለጫው የተሰጠው፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫ በ3 መሰረታዊ አጀንዳዎች ላይ መሰረት ያደረገ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አፈፃፀም፣ በኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ የአአ እጩ ውክልና እና ቀጣይ ስራዎች ላይ ነበር፡፡

አስቀድመው የመጀመርያ አጀንዳውን በመግለፅ ንግግር ያደረጉት አቶ በለጠ ዘውዴ የዘንድሮ የአአ ከተማ ዋንጫ በሁሉም ረገድ የተሳካ እንደነበረ ገልፀው ከተመልካች ገቢ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ ይህ ገቢ እስካሁን ከተዘጋጁ ውድድሮች ሁሉ ከፍተኛ ገቢ እንደሆነ ተገለፀ ሲሆን በድምሩ ከ160 ሺህ በላይ ተመልካች ታድመውበታል። በአጠቃላይ የአአ ዋንጫ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሻለ አፈፃፀም የታየበት ሆኖ መጠናቀቁን የገለፁት አቶ በለጠ የመዝጊያው ጨዋታ ላይ ከስፖርታዊ ጨዋነት ችግር ጋር ተያይዞ አላስፈላጊ ችግር የተፈጠረ ቢሆንም በተደረገው ከፍተኛ ጥረት ጨዋታው ሳይቋረጥ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ተደርጓል ብለዋል።

የውድድሩ ስኬተማነት ምስጢር ምንድን ነው ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ የስራ አስፈፃሚ አባላት ከተለያዩ ኮሚቴዎች ጋር በጋራ ተቀናጅተው በመስራታቸው፣ መረጃዎችን በፍጥነት ለሚዲያው እንዲደርስ ማድረጋችን፣ ውድድሩ ፉክክር እንዲኖረውና ተመልካች ወደ ሜዳ እንዲመጣ ለመሳብ ያዘጋጀናቸው የሽልማት አይነቶች ለምሳሌ በየጨዋታው የኮኮቦች ምርጫ ሌሎች የተቀናጀ ስራዎችን በመስራታችን ለተገኘው ስኬት አስተዋፆ ነበራቸው።›› ብለዋል፡፡

አቶ በለጠ አክለውም ከዚህ ቀደም በተደረገው ስምምነት መሰረት ለክለቦች የገቢ ክፍፍል እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ከዚህ ቀደም ክለቦችን ቅር ያሰኛቸው ጉዳዮች ዘንድሮ እንዳይፈጠር በማሰብ ከተገኘው ገቢ ከወጪ ቀሪ ከክለቦች ጋር በሚገባ ተነጋግረን ወደፊት የምንገልፀው ይሆናል። ገንዘቡም ከክለቦች ጋር ባደረግነው ስምምነት መሰረት ገቢ ይደረግላቸዋል›› ብለዋል ።
የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን በስሩ በርካታ ውድድሮች እያወዳደረ የሚገኝ ሲሆን ሌሎች የከተማው እግርኳሳዊ ስራዎችንም ይሰራል፡፡ በአአ ከተማ ዋንጫ የተገኘውን ከፍተኛ ገቢ በመጠቀምም ካለፉት ጊዜያት የተሸለ ስራ ይሰራል ተብሏል፡፡ ‹‹የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዘንድሮ በርካታ ስራዎችን ለመስራት አስቧል የውስጥ ውድድሮቻችንን በተቀናጀ ሁኔታ የማካሄድ፣ የእግርኳስ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣ የአቅም ማሳደጊያ ስልጠናዎችን መስጠት ፣ እንዲያውም የአአ ቡድኖች በሆኑት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ፣ የከፍተኛ ሊግ ቡድኖች መካከል ውድድሮችን ለማዘጋጀት አስበን ነበር፡፡ ሆኖም በቂ የማጫወቻ ሜዳ ባለማግኘታችን ሳናከናውን ቀርተናል፡፡ በቀጣይ ከወዲሁ ተዘጋጅተን ውድድሩን እናደርጋለን›› ሲሉ አቶ በለጠ አብራርተዋል፡፡

በቀጣይ በሁለተኛው አጀንዳ ዙርያ ጋዜጣዊ መግለጫው ቀጥሏል፡፡ ፌዴሬሽኑ ባቀረባቸው እጩ ላይም ዘመቻ እየተከፈተ እንደሆነ ተገልጧል፡፡  ‹‹ የአአ እጩ ሆነው በቀረቡት ኢ/ር ኃይለየሱስ ፍስሀ ላይ የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን ስም እና ክብር የሚያጎድፍ ዘመቻ እየተፈፀመ ይገኛል። ከዚህ በኋላ በዝምታ አናየውም፡፡ ይህን ዘመቻ በከፈቱት ላይ አስፈላጊውን ማስረጃ እያሰባሰብን ነው፡፡ በህግ የምንሄድበት ይሆናል፡፡›› ተብሏል፡፡ ፌዴሬሽኑ የአአ አሰልጣኞች ማህበር ኃይለየሱስ ፍስሀ የዲሲፕሊን ችግር አለባቸው ፣ የስፖርት ባለሙያ አይደሉም በማለት ያስገቡት ደብዳቤ እንዳሳዘነውም ተገልጧል፡፡

የአአ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቀረቡለት እጩዎችን ለመምረጥ ሦስት መስፈርቶችን ያወጣ ሲሆን እነዚህም 1ኛ. የትምህርት ደረጃ 2ኛ. በስፖርቱ ያለፉ መሆናቸውን ማረጋገጥ 3ኛ. ለአአ እግርኳስ ያበረከቱትን አስተዋፆ መገምገም እንደሆነ እና በዚህ መሰረት ኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በስራ አስፈፃሚነት ቢመረጡ የተሻለ ስራ ሊሰሩ ይችላሉ ብሎ በማሰብ ኢ/ር ኃይለየሱስ መመረጣቸው ተገልጧል፡፡

በምርጫው ዙርያ ከጋዜጠኞች የቀረቡ ጥያቄዎች እና የተሰጡ ምላሾች

የፕሬዝዳንት እጩ ፌዴሬሽኑ ለምን አላቀረበም ?

ይህ ቦታ ከዚህ ቀደምም ቢሆን አአ እጩ አላቀረበም፡፡ ዘንድሮም ቢሆን ለፕሬዝደንትነት ልወዳደር ብሎ የጠየቀን የለም።

አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ የእጩ ጥያቄ በተመለከተ ?

የአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ጉዳይን በተመለከተ በቀጥታ ጥያቄው በደብዳቤ ለእኛ መላክ ሲገባው ለኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የቀረበ በመሆኑ አልደረሰንም ነበር የአካሄድ ስህተት ቢኖረውም እንኳ በግልባጭ የደረሰንን ደብዳቤ ተመልክተን ባወጣነው መስፈርት መሰረት የተሻሉ የሆኑትን ኃይለየሱስ ፍስሀን መርጠናል፡፡

ያላግባብ ስም አጠፉ የተባሉት እነማን ናቸው?

በዋናነት የአአ አሰልጣኞች ማህበር ነው፡፡ ለኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያስገቡት ደብዳቤ እንደሚያሳየው ከኦዲት ኮሚቴ የተነሱት በዲሲፒሊን እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ይህ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀድሞ ስራ አስፈፃሚ የነበሩም ሌሎች ግለሰቦች አሉ ወደፊት ይገለፃሉ። አሁን እኛ እንደ ተቋም የተነሱት በዲሲፒሊን እንዳልሆነ የሰነድ ማስረጃ አለን፡፡ ይህን ይዘን ወደ ህግ እንሄዳለን ፣ ግለሰቡም በግላቸው ወደ ህግ ያመራሉ።

ሌሎች ለተጠየቁ ጥያቄዎች በሌሎች አካላት ምላሽ የተሰጠ ሲሆን በሦስተኛነት ተይዞ የነበረው አጀንዳ ለጋዜጠኞች ማብራርያ ሳይሰጥበት ጋዜጣዊ መግለጫው ፍፃሜውን አግኝቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *