​ኢምፓክት ሶከር ወደ አካዳሚነት…

ከ15 በላይ ዕድሜ ያለው እና ምስረታውን በሀገረ አሜሪካ ሜሪላንድ ላይ ያደረገው ሶከር ኢምፓክት የእግር ኳስ አካዳሚ የዕድሜያቸው ከ14 አመት በታች የሆኑ በቁጥር 50 የሚደርሱ አሜሪካዊያንን እንዲሁም የካናዳ ፣ የኔዘርላንድ እና የሌሎች ሀገራት ታዳጊ ተጫዋቾችን አካቶ ነበር ስራ የጀመረው። አካዳሚው ከ30 አመት በፊት ከኢትዮጵያ በወጡት እና የኢንጅነሪንግ ባለሙያ በሆኑት አቶ ያሬድ አማኑኤል አማካይነት የተቋቋመ ነበር። ግለሰቡ በጊዜው ምንም እንኳን በእግር ኳሱ ጠልቅ ያለ እውቀት ባይኖራቸውም ኃላ ላይ በወሰዱት የአሜሪካ የስልጠና ላይሰንስ አማካኝነት እስከ ኢንስትራክተርነት ደረጃ በመድረስ ወደ ስራው ገብተዋል። አቶ ያሬድ በነዚህ አመታት በዘርፉ ያካበቱትን ተሞክሮ ይዘው ነበር ከአንድ አመት በፊት ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት።

ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ጥናት በማድረግ ላይ ሳሉ ከአሰልጣኝ መሰረት ማኒ ጋር ሜሪላንድ ላይ የተገናኙት አቶ ያሬድ በነበራቸው ቆይታ በሀገሪቱ እግር ኳስ እድገት የወደፊት መሰረት በሆኑት ታዳጊዎች ላይ መስራት የተሻለ ሀሳብ መሆኑን ተረዱ። በዚህ መሰረትም አቶ ያሬድ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ድሬዳዋ ላይ በአሰልጣኝ መሰረት ማኒ መሪነት እና በሌሎች አራት አሰልጣኞች እገዛ ስራቸውን ጀመሩ። ስራው በአቶ ያሬድ ድጋፍ ለአንድ ዐመት ቢቆይም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፕሮጀክቱን በግሉ በመያዙ ፕሮጀክቱን ወደ ትልቅ አካዳሚነት ቀይሮ ለመገንባት ሀዋሳ ከተማን ምርጫው አድርጓል።

ሀዋሳ የብዙ እግር ኳስ ተጫዋቾች መገኛ መሆኗን በማመን ከ8 ወራት በፊት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቶ ያሬድ  ወደ ሀዋሳ ወጥተዋል። በጅምሩም ከየአካባቢው የተወጣጡ በድምሩ 100 የሚሆኑ ሴት እና ወንድ ታዳጊዎችን በመያዝ ፕሮጀክቱ ኢምፓክት ሶከር ሀዋሳ  ተብሎ ተመሰረተ።

ትውልደ ኢትዮጵያዊውን አቶ ያሬድ ያመጡትን ይህን ትልቅ አላማ ለማገዝም አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ፣ ኢንስትራክተር አለምባንተ ማሞ እና አሰልጣኝ መልካሙ ታፈራ ያካተተ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ልጆቹን የሚያሰለጥኑ ተጨማሪ አሰልጣኞችም ተካተው ፕሮጀክቱ ስራውን ጀምሯል። አቶ ያሬድ አንድ ጃፓናዊ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝን የቀጠረ ሲሆን 200 ሺህ ዶላር በማውጣት ለልጆቹ የመጫወቻ ኳስ እና ትጥቆችን እንዲሁም ለስልጠናው የሚጠቅሙ ቁሳቁሶችን በመለገስ ከ6 ወራት በፊት ወደ አሜሪካ ተመልሷል። ባሳለፍነው ማክሰኞ ዳግም ሲመለስም ይህን ፕሮጀክት ወደ አካዳሚነት ለማሳደግ ከሀዋሳ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ታምሩ ታፌ ጋር እና ሌሎች አካላት ጋር ንግግር በማድረግ ለግንባታው  ፍቃድ አግኝቷል።

ዘመናዊ የመጫወቻ ሜዳ ፣ የመኖሪያ ቤቶች ፣ የመማሪያ ክፍሎች እና የመዝናኛ ስፍራ በውስጡ ያካተተው የአካዳሚው ዲዛይን ተጠናቆ በቅርብ አመት ውስጥ ወደ ስራ እንደሚገባም ይጠበቃል። አካዳሚው ተጠናቆ በራሱ እስኪቆም ድረስም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ላይ ልምምድ እየሰሩ የሚቀጥሉ ይሆናል። ባሳለፍነው አርብ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ በተካሄደ ፕሮግራም አቶ ያሬድ  ይዘውት የመጡትን ትጥቆች እና የላብ መተኪያዎች ለታዳጊዎቹ አከፋፍለዋል። ሰልጣኞቹ በእለቱ የተደረገላቸው ድጋፍ ደስ እንዳሰኛቸው እና ይህ አካዳሚ ተጠናቆ ለማየት እንደጓጉ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አሰተያየት ተናግረዋል ።

አቶ ያሬድ አማኑኤል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ “ሀገሬን በጣም እወዳለሁ። የእግር ኳሱም ፍቅር ስላለኝ ነው ይህን የማደርገው። ኢትዮጵያ ታለንት ያለባት ሀገር ናት። ይህ ነገር ብቻዬን እወጣለሁ ብዬ አላስብም። እገዛ ያስፈልገኛል። በተለያየ ጊዜ ስራ ስላለኝ ከሀገር እወጣለው። ግን እዚህ ያደራጀዋቸው ኮሚቴዎች ስላሉ ያግዙኛል። እኔም ሄጄ የተወሰነ ገንዘብ ሰብሰብ አድርጌ ፈሰስ አደርጋለሁ። እቅዴ ሰፊ ነው። አካዳሚው ተገንብቶ ማየት ህልሜ ነው። ሀዋሳን ስመርጥ የብዙ እግር ኳስ ተጨዋቾች ምንጭ በመሆንቀዳሚ ናት ብለን ነው። አካዳሚው ሲያልቅ ግን በየሀገሩ ያሉ ታዳጊዎችን አምጥተን ወደዚህ እናስገባለን። ሀዋሳ ማዕከል ትሁን እንጂ  በቀጣይ በብዙ ከተሞች ፕሮጀክት እንመሰርታለን። ጥሩ የሚሆኑትን እያመጣን ወደ ሀዋሳ እናስገባለን። አሁን የረዱኝን ሁሉ አመሰግናለሁ። በቀጣይ በጋራ የኢትዮጵያን ኳስ ከታች ሰርተን እንለውጣለን” ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *