ኮንፌድሬሽን ዋንጫ፡ “እቅዳችን ዚማሞቶን አሸንፈን ለቀጣይ ዙር መዘጋጀት ነው” ዘነበ ፍስሃ

በ2018 ቶታል ኮፍ ኮንፌድሬሽን ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ የሚያደረገው ወላይታ ድቻ ከዛንዚባሩ ዚማሞቶ ጋር ላለበት ጨዋታ ትላንት ጠዋት ወደ ስፍራው አቅንቷል፡፡ ሁለቱም ክለቦች በኮንፌድሬሽን ዋንጫ ሲሳተፉ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ዚማሞቶ አምና በቻምፒየንስ ሊጉ ተሳትፎ አድርጎ እስከምድብ መጓዝ በቻለው የሞዛምቢኩ ፌራቬዮሮ ደ ቤይራ 4-3 የአጠቃላይ ውጤት ተሸንፎ ከውድድር ወጥቷል፡፡

በፕሪምየር ሊጉ ወላይታ ድቻ ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች በመልካም አቋም ላይ ከመገኘቱ ባሻገር ሶስት ጨዋታዎችን ድል አድርጎ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል፡፡ ቡድኑን ለረጅም ጊዜያት ያሰለጥኑት መሳይ ተፈሪ ጋር ድቻ ከተለያየ በኃላ የአሰልጣኝነት መንበሩን የተረከቡት ዘነበ ፍስሃም ከቡድኑ ጋር የተሻለ ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ አሰልጣኝ ዘነበ ስለወላይታ ድቻ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ እቅድ፣ የቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ እና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ስለድቻ ለውጥ እና ዝግጅት

እኔ የተረከብኩት ቡድኑ 16ኛ ሆኖ እያለ ነበር፡፡ በቅርብ ቡድኑን ስከታተል ስለነበር እና የተጫዋቾቹን አቅም በራሴ እይታ እየገምገምኩ ነበር፡፡ ተጫዋቾቹ ያላቸው አውጥተው እንዲጫወቱ ባላቸው ላይ ነው ስራዎችን ስንሰራ የነበረው፡፡ ያላቸውን አቅም ይዘው ጠብቀው አሳድገው እንዲሄዱ ነው የሰራነው፡፡ እኔ ከመጣሁ በኃላ ከኳስ ጋር ነው በይበልጥ ትኩረት ሰጥተን የሰራነው፡፡ በራስ መተማመናቸው እንዲያድግ፣ አንድነት እና ፍቅር እንዲኖራቸው ለማድረግ ስራ ሰርተናል፡፡ ለውጦቹ እንዚህ ብቻ ሳይሆኑ የታክቲክ ለውጥ ነበር፡፡ በታክቲካል ለውጡ ብዙም ድካም ሳይኖር ሁሉም ተመሳሳይ አይነት ድካም ደክመው እንዳይወጡ ተጋግዘው እንዲጫወቱ እንችላለን የሚለው ነገር በውስጣቸው እንዲሰርፅ ለማድረግ ነው ሳሰራ የነበረው፡፡

ሱሉልታ ከዛንዚባር ዓየር ጋር ተቀራራቢነት ስላለው ልምምዳችን እዛው አድርገናል፡፡ ሙቀት እንደሆነ እና ወደ 32 ዲግሪ ሴትቲግሬድ እንደሆነ ሰምተናል። በዚህም ሃዋሳ ለመስራት አስበን ነበር፡፡ ንፋስ እና ቀዝቃዛ ዓየርም አለ ስለተባለ ሱሉልታ ሄደን ብንሰራ የተሻለ ነው በሚል ተነጋግረን ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣነው፡፡ በሱሉልታ አንድ ቀን ሰርተናል፡፡ አየሩ በጣም ከባድ እና አስቸጋሪ ነበር፡፡ ተጫዋቾቹም ትንሽ ተቸግረዋል፡፡ እኛም አየሩን እንዲላመዱ ትንሽ ጫን አድርገን ልምምድ ሰጥተናል፡፡ እዛ መስራታችን ለዛንዚባሩ ጨዋታ ይረዳናል ብዬ አስባለው፡፡

የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለመሳተፍ እና ስለተጋጣሚቸው

እኛ ተስፋ ያደረግነው ተጋጣሚያችን ዚማሞቶ ልክ እንደኛ ለውድድሩ አዲስ መሆኑ ነው፡፡ ብዙም የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ እንደሌለው መረጃዎች ደርሰውናል፡፡ እኛም የዚማሞቶን ጨዋታ የሚያሳይ ምስል አግኝተን ለመመልከት ችለናል፡፡ በአካል ብቃት ደረጃ ጥሩ ናቸው፡፡ የሚጫወቱበት መንገድንም ምን ይመስላል የሚለው አይተናል፡፡ በእዚህ ላይ ተመርኩዘን ስራዎችን ሰርተናል፡፡
እንግዳ እንደመሆናችን ልምድ ወሳኝ ነው፡፡ ለእግርኳስ ልምድ ወሳኝ ነው፡፡ እኛ ጋር አረፋት ጃኮ ነው ልምድ ያለው ሊባል የሚችለው፡፡ ተጫዋቾቹ በአንድነት እና በህብረት እንዲጫወቱ ነው የምንፈልገው፡፡ አዲስ ነገር እንደሌለ እና ሜዳ ላይ የሚያጋጥሙ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ነግረናል፡፡ በስነ-ልቦናም ብዙ ነገር ተነጋግረናል፡፡ ጥሩ መነሳሳት ስላለ ብዙም አይቸገሩም ብዬ አስባለው፡፡

የመጀመሪያ ጨዋታ እቅድ

በመጀመሪያው ጨዋታ ጥሩ ተፎካካሪ ሆነን ዚማሞቶን አሸንፈን ለቀጣይ ውድድር ለመዘጋጀት ነው እቅዳችን፡፡ ይህንን ውድድር በተቻለ መጠን በጥንቃቄ እየተንቀሳቀስን ውጤት ይዘን ለመምጣት ነው፡፡ አቻ የሚባል ነገር አይደለም የምናስበው ፤ በሜዳቸው አሸንፈን ለመመለስ ነው፡፡ ያንን ለማድረግ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ እና በትኩረት ተንቀሳቅሰን ዚማሞቶን በሜዳው አሸንፈን ለመመለስ ነው፡፡ በተጫዋቾቹ መሃል ያለው ነገርም ጥሩ ነው። አሸንፈን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *