ጋቶች ፓኖም መቐለ ከተማን ተቀላቀለ

ለስድስት ወራት በሩሲያው አንዚ ማካቻካላ ቆይታ አድርጎ ወደ ሀገር ቤት የተመለሰው ጋቶች ፓኖም ከተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ክለቦች ጋር ስሙ ሲያያዝ ቆይቷል።

ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ከቀድሞው ክለቡ ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ወላይታ ድቻ ጋር ያደረጋቸው ድርድሮች ዳር ሳይደርሱ ቀርተዋል። ተጨዋቹ ወደ ደቡብ አፍሪካው ቢድ ቬስት ዊትስ ለሙከራ አቅንቶም የተሳካ ጊዜ ቢያሳልፍም በክለቡ የሚገኙ የውጪ ዜጎች ቁጥር ኮታ በመሙላቱ እና በሱ ምትክ ሊለቁት የነበረው ተጨዋች ባለመልቀቁ ሳይፈርም መቅረቱን ወኪሉ ዴቪድ በሻህ ገልጿል።

ትላንት ከደቡብ አፍሪካ የተመለሰው ጋቶች ዛሬ ከሌላኛው የፕሪምየር ሊጉ ክለብ መቐለ ከተማ ጋር የተሳካ ድርድር አድርጎ የአንድ አመት ኮንትራት የተፈራረመ ሲሆን የአለምአቀፍ የዝውውር ሰርተፍኬቱ ከጠናቀቀ በኃላ በሁለተኛው ዙር የመቐለን መለያ ለብሶ የምንመለከተው ይሆናል። ሆኖም ግን ቢድ ቬስት ዊትስ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ተጨዋቹን መልሶ የማግኘት ፍላጎት ያለው በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ከመቐለ ጋር ያለው ስምምነት ምን እንደሆነ አልታወቀም።

በተያያዘ ዜና ለአንድ ወር በሙከራ ላይ የነበሩት ካርሎስ ዳምጠው እና እያሱ በቀለም ሙከራውን በስኬት በማጠናቀቅ የአንድ አመት ኮንትራት ፈርመዋል። ካርሎስ መከላከያን ከለቀቀ በኃላ በዘንድሮው የውድድር አመት አማራ ውሃ ስራን ተቀላቅሎ ያለፉትን ወራት የቆየ ሲሆን የቀድሞው የደደቢት ተከላካይ እያሱ ደግሞ በሞልዶቫ እና ቡልጋሪያ የአጭር ጊዜ ቆይታ አድርጎ ተመልሷል። በተጨማሪም ሁለት ተጨዋቾችን ከቢው ቡድን ማሳደጉ ታውቋል።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *