ወላይታ ድቻ በታሪኩ የመጀመርያ በሆነው የቶታል ካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳትፎው በቅድመ ማጣርያ ጨዋታ የዛንዚባሩ ዚማሞቶን በደርሶ መልስ ባስመዘገበው ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ችሏል። ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ በሚደረገው የአንደኛ ዙር የወላይታ ድቻ ተጋጣሚ የሆነው ደግሞ የግብፁ ታላቅ ክለብ ዛማሌክ ነው።
የግብፅ ፕሪምየር ሊጉ ክለብ ፔትሮጄትን በአምበልነት እየመራ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ሽመልስ በቀለ በግብፅ ቆይታው በተደጋጋሚ ዛማሌክን የገጠመ ሲሆን የጨዋታው እውን መሆንን ተከትሎ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ቻምፒየንስ ሊጉን ከ2002 ወዲህ ማሳካት የተሳነው ዛማሌክ በአሁኑ ወቅት ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ እንዳልሆነ ገልጿል። ” ዛማሌክ ያን ያህል ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ አይደለም። ያለፉትን ሦስት አመታት አቋሟቸው ወርዷል። የሊጉን የበላይነት አል አህሊ ተቆጣጥሮታል። የዛማሊክ ወቅታዊ አቋሙ ጥሩ አለመሆኑ እንደምክንያት የሚቀርበው በየጊዜው የአሰልጣኝ ለውጥ ማድረግ እና በተለያየ ጊዜም አዳዲስ ተጨዋቾች እየመጡ ከቡድኑ ጋር መቀላቀል ነው። ተጨዋቾቹ አንድ ላይ ቶሎ የመቀናጀት ችግር አለባቸው ፤ በዚህም በሊጉ ወጣ ገባ አቋም እንዲኖረው እድርጎታል። ሰሞነኛ አቋሙ ዛማሌክ ጥሩ አይሁን እንጂ ሁሉም እንደሚያቀው በአፍሪካ ካሉ ክለቦች በታሪክም በብዙ መንገድ ጠንካራ ቡድን መሆኑ ነው። ”
የጦና ንቦች በውድድሩ የመጀመርያ ተሳትፏቸው በአህጉሪቱ የገዘፈ ስም ካላቸው ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ቡድን ከፊታቸው ቆሟል። ምንም እንኳን በጥሩ አቋም ላይ ባይገኝም በ2016 ለፍፃሜ የደረሰ መሆኑን ስናስታውስ የስነ-ልቦና የበላይነቱን እንደሚወስድ ይታመናል። ሽመልስ በቀለም የስነልቦና ጉዳይ ድቻ በዋነኝነት ትኩረት ሊያደርግበት የሚገባው ጉዳይ መሆኑን ገልጿል። ” ዛማሌክ ከባድ ተጋጣሚ ቢሆንም ወላይታ ድቻዎች በስነ-ልቦናው ራሳቸውን በሚገባ አዘጋጅተው አጠናክረው ከተዘጋጁ በቅድመ ማጣርያው ዙር ያገኙትን ውጤት እዚህም ያገኛሉ ብዬ አስባለው። ግብፅ ላይ ሲጫወቱ ይከብዳቸዋል ብዬ የማስበው የዛማሌክ ደጋፊ ነው። ደጋፊዎቻቸው በተቃራኒ ቡድን ላይ የሚያሳድሩት ጫና ከፍተኛ ነው። በድቻ ሁሉም ተጫዋቾች በከፍተኛ ደጋፊ መሐል በኢንተርናሽናል ጨዋታ ጫና ተቋቁሞ የመውጣት ልምድ ላይኖራቸው ይችል ይሆናል ፤ ይህ እንዳይከብዳቸው እሰጋለው። ሆኖም የራሳቸውን አጨዋወት ይዘው ከገቡ እና እንደ ቡድን ከተንቀሳቀሱ ብዙም ይቸገራሉ ብዬ አላስብም። ዋናው ግን በስነ ልቦናው ረገድ በደንብ ሰርተው ቢመጡ እና ቡድኑን አግዝፈው ባይመለከቱ መልካም ነው። ” ብሏል።
በሁለቱም ቡድኖች መካከል የሚደረገው የአንደኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታ በመጋቢት ወር የመጀመርያ ቀናት ሀዋሳ ላይ ሲካሄድ የመልሱ ጨዋታ ከመጋቢት 10-12 የባሉት ቀናት ኣይሮ ላይ የሚደረግ ይሆናል። መቀመጫውን ከካይሮ የ2 ሰአት የመኪና መንገድ ርቀት ላይ በምትገኘው ሱኤዝ ከተማ ያደረገው ፔትሮጄት አማካይ ሽመልስ በቀለም በስታድየም ተገኝቶ ለወላይታ ድቻ ድጋፉን ለመስጠት እንደተዘጋጀ ገልጿል።
” በሚገባ ቡድኑን አበረታታለሁ። እኔም ብቻ ሳልሆን ከኡመድ ጋር በመሆን ቡድኑን ለማገዝ ጨዋታውን እንከታተላለን። ይህን በጣም የምንናፍቀው ነገር ነው። ምክንያቱም ወላይታ ድቻ የሚወክለው ኢትዮዽያን በመሆኑ ከኡመድ ጋር በመሆን በሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን በምንችለው መጠን ለማገዝ ዝግጁ ነን። “