​ወልዲያ ተጫዋቾቹን ለማገድ ተቃርቧል

በወልዲያ እና በሦስት የቡድኑ ተጫዋቾች ወደ ክለቡ አለመቀላቀል ዙርያ የተፈጠረው ውዝግብ የመጨረሻ ውሳኔ ሊያገኝ ተቃርቧል።

ወልዲያ ስፖርት ክለብ ካጋጠመው ወቅታዊ ችግር ተላቆ በአሁኑ ወቅት በተረጋጋ ሁኔታ በተከታታይ ለሚጠብቁት አራት ተስተካካይ ጨዋታዎች ዝግጅቱን በተጠናከረ መልኩ የቀጠለ ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ የመጀመሪያ ተስተካካይ ጨዋታውን ከኢትዮ ኤሌትሪክ ጋር በሼህ መሀመድ ዓሊ አላሙዲን ስታድየም 09:00 ላይ እንደሚያደርግ ይጠበቃል። ሆኖም አብዛኛው የቡድኑ አባላት ለቀጣይ ጨዋታዎች ተሰባስበው መደበኛ ልምምዳቸውን እየሰሩ በሚገኙበት በአሁኑ ሰአት ፍፁም ገ/ማርያም ፣ ያሬድ ብርሃኑ እና ወደ አሜሪካ የተጓዘው ታደለ ምህረቴ ቡድኑን አለመቀላቀላቸውን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል ።
ይህን ተከትሎም የክለቡ የቦርድ አመራሮች ከሰሞኑን ባደረጉት ስብሰባ ተጨዋቾቹ በአስቸኳይ ቡድኑን እንዲቀላቀሉ በደብዳቤ የገለፁ ሲሆን ደብዳቤውን ተቀብለው ከቡድኑ ጋር የማይቀላቀሉ ከሆነ በክለቡ መተዳደርያ ደንብ መሰረት ለሁለት አመታት ሊታገዱ እንደሚችሉ ሰምተናል።

ቡድኑን ያልተቀላቀሉት ሦስቱ ተጨዋቾች ምክንያታቸው ምን እንደሆነ እና ያላቸውን ሀሳብ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ያልተሳካ ቢሆንም ታደለ ምህረቴ ወደ አሜሪካ በማቅናቱ ከዚህ በኋላ ቡድኑን ይቀላቀላል ተብሎ የማይጠበቅ ሲሆን በተመሳሳይ ፍፁም ገ/ማርያም እና ያሬድ ብርሃኑም እንደማይመለሱ እየተሰማ ይገኛል ።  ይህ የሚሆን ከሆነ ክለቡ እወስነዋለው ያለው የሁለት አመት ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችል ይጠበቃል ።

ወልድያ ተስተካካይ ጨዋታዎቹን እየጠበቀ በደረጃ ሰንጠረዡ 11 ነጥብ በመያዝ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲገኝ በሁለተኛው ዙር ደረጃውን አሻሽሎ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ይረዳው ዘንድ እስከ ስምንት የሚደርሱ አዳዲስ ተጨዋቾች ለማስፈረም በዝውውር ገበያው ላይ ሊንቀሳቀስ እንደሚችል ከክለቡ አካባቢ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *