​ሐብታሙ ተከስተ ስለ እግርኳስ ህይወቱ ይናገራል

በሊጋችን ላይ የሚታዩ አዳዲስ ፊቶችን በየሳምንቱ ወደ እናንተ ማድረሳችንን ቀጥለናል። የዛሬው እንግዳችን በመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ የውድድር አመቱ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያሳየ የሚገነው የመቐለ ከተማው አማካይ ሐብታሙ ተከስተ ነው።  ሐብታሙ ስለ እግርኳስ ህይወቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገውን ቆይታ እነሆ።

ትውልድና እድገትህ የእግርኳስ ተጨዋችነት መነሻህ እንዴት ነው ?

ትውልድ እና እድገቴ ጎንደር ከተማ ነው። ከቤተሰቤ መካከል እግርኳስን ተጫውቶ ያለፈ ባይኖርም ፋሲል ከተማ ሲጫወት ስታድየም በመግባት እከታተል ነበር። ከዛ ጀምሮ እግርኳስ ተጫዋች የመሆን ጉጉት እና ፍላጎት እያደረብኝ መጣ። እድሜዬ ለእግርኳስ ተጨዋችነት ሲደርስ በጎንደር ከተማ ውስጥ ጎንደር የሚባል ፕሮጀክት ውስጥ ገብቼ መሰልጠን ጀመርኩ።

በፕሮጀክት ስለነበረህ ቆይታ እና በቀጣይ ከፕሮጀክቱ በኋላ ስላለው ሁኔታ ንገረን?

የእግርኳስ ክህሎቴን ያሳደኩበት እና መሰረት የጣልኩበት ጊዜ ነው በፕሮጀክት ያሳለፍኩት። ዳሽን ቢራ በ2006 ወደ ፕሪምየር ሊግ ባደገበት አመት ወደ ተስፋ ቡድኑ አምርቼ የመጫወት እድል አግኘው ።  ለአንድ አመት ከሰባት ወር በዳሽን ተስፋ ቡድን ከቆየው በኋላ በከፍተኛ ሊግ ለሚወዳደረው ለሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሀን ለሦስት ወር ያህል መጫወት ችያለው ። ከዚህ በኋላ ዳሽን ቢራ 2008 ሲፈርስ በቀጥታ አምና ወደ መቐለ ከተማ አምርቼ ይሄው እስካሁን በመጫወት ላይ እገኛለው።

መቐለ ከተማ ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ እንዲገባ ካስቻሉ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ነህ። የአንተም ሆነ የክለብህ የከፍተኛ ሊግ የውድድር አመት ጉዞ ምን ይመስል ነበር ?

የአምናው የከፍተኛ ሊግ በጣም ከባድ ነበር። ለእኛም የመጀመርያችን ስለነበር በጣም ከብዶን ነበር። አሰልጣኙ እና ተጫዋቾች መካከል መልካም ግኑኝነት የነበረ በመሆኑ በስኬት በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ወደ ኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ልንገባ ችለናል። እኔም በግሌ ብዙ ነገር የተማርኩበት እና ልምድ ያገኘሁበት ጥሩ የውድድር ጊዜ ነበር። በአመቱ ውስጥ ከተካሄዱ 31 ጨዋታዎች በ25ቱ ጨዋታ ላይ በመጀመርያ ተሰላፊነት ተጫውቻለው ፣ ሰበታ እና ሽሬ ላይ ሁለት ጎል ያስቆጥሬያለው ። በአጠቃለይ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍኩበት አመት ነበር።

መቐለ ከተማ አሁን በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ እየተወዳደረ ይገኛል። አምና ብዙ ጨዋታ ከማድረግህ አንፃር በመጀመርያዎቹ የቡድኑ ጨዋታዎች ላይ ከመጀመርያ አሰላለፍ ውጪ ነበርክ። አሁን ደግሞ በመደበኝነት እየተሰለፍክ ትገኛለህ።  በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች ላይ ያልነበርከው በምን ምክንያት ነው? አሁን ያለህን አቋምስ እንዴት ታየዋለህ? 

ዘንድሮ ከውድድሩ መጀመር አስቀድሞ በዝግጅት ወቅት ጉዳት ላይ የነበርኩ በመሆኔ ምክንያት መጫወት አልቻልኩም። ከጉዳትም እንደተመለስኩ በፍጥነት አቋሜ ተስተካክሎ ለጨዋታ ብቁ መሆን አልቻልኩም ነበር። ቀስ በቀስ ራሴን እያስተካከልኩ በተወሰኑ ጨዋታዎች ላይ ከተቀያሪ ወንበር እየተነሳው መጫወት ጀመርኩ። ከሰባተኛው ሳምንት ጀምሮ ግን እስካሁን ወደ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ገብቼ በጥሩ ሁኔታ ክለቤን እያገለገልኩ እገኛለሁ።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ በምጣት እድገትህን እያሳየኸን የምትገኘው። ይህን እድገትህን አስጠብቀህ ለመዝለቅ በቀጣይ ምን ታስባለህ?

የሁሉም ተጫዋች ምኞት ራሱን በተሻለ ነገር አሳድጎ ከሀገር ውስጥ አልፎ በውጭ ሀገር መጫወት ነው። እኔም ከዚህ በተሻለ ራሴን ከእለት ወደ እለት አሻሽዬ በብሔራዊ ቡድን እና በውጭ ሀገርም መጫወት አስባለው። አሁን ሩጫዬን ጀመርኩ እንጂ አልጨረስኩም። በቀጣይ ጠንክሬ በመስራት ራሴን የተሻለ ደረጃ ማድረስ እፈልጋለው።


ስም – ሐብታሙ ተከስተ

የትውልድ ዘመን – 1987

የትውልድ ስፍራ – ጎንደር

የሚጫወትበት ቦታ – አማካይ

ቁመት – 1.86 ሜትር

ክብደት – 62 ኪ.ግ.

ክለብ – መቐለ ከተማ


በሁለቱ የሊግ እርከኖች ተጫውተሀል። በፕሪምየር ሊግ እና የከፍተኛ ሊግ መካከል ያሉትን ልዩነቶች እንዴት ታያቸዋለህ?

በጣም ልዩነት አለው። ከፍተኛ ሊግ በጣም ጉልበት የበዛበት እና ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ ነው። እዛ ለመጫወት ይከብዳል። ፕሪምየር ሊግ ግን ብዙ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች አሉ። ከእነሱ ጋር ሆነ ስትጫወት ይቀልሀል። ከዚህ በተጨማሪ የመጫወቻ ቦታ ክፍተት አለው። በሁሉም ረገድ ካየኸው ፕሪምየር ሊጉ ላይ መጫወት ጥሩ ነገር አለው ብዬ አስባለሁ።

የተከላካይ አማካይ ሆኖ መጫወት የሚጠይቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ። አንተም በቦታው የብቃትህ ጫፍ ለመድረስ ምን የተለየ ነገር ትሰራለህ?

ብዙ ጊዜ እዚህ ቦታ ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በተክለ ሰውነታቸው ረዘም ያሉ ቢሆን ይመረጣል ይባላል። ለእኔም ረዘም ማለቴ አስተዋጽኦ አድርጎልኛል ብዬ አስባለው። ዋናው ነገር በአዕምሮህ ላይ የምትሰራው ትልቁን ቦታ ይወስዳል። ከዚህ ውጭ በትንፋሽ ረገድ የማልቸገር ቢሆንም በአሰልጣኛችን ከሚሰጠን ስልጠና በተጨማሪ በግሌ ልምምዶችን እሰራለው።

የመቐለ ከተማ የፕሪምየር ሊግ ጉዞን እንዴት አየኸው?

እንደምታዩት በጥሩ ደረጃ ላይ ነው የምንገኘው። ይህ ደግሞ አሰልጣኙ የሚሰጠንን ስልጠና እና ትዕዛዝ በሚገባ መተግበራችን እና በተጫዋቾች መካከል ያለን ጥሩ ግኑኝነት ለውጤት ማማር ማማር አስተዋፆኦ አለው።  በቀጣይም ባሉብን ክፍተቶች ላይ ማሻሻያ አድርገን በጥሩ ደረጃ ሊጉን ማጠናቀቅ እንፈልጋለን ።

ለእኔ ምሳሌ ነው የምትለው ተጫዋች ማነው? 

ለእኔ ምሳሌ የሆነኝ ተጨዋች አስራት መገርሳ ነው። በዳሽን ቢራ ተስፋ ቡድን ቆይታዬ ከዋናው ቡድን ጋር አብሮ የመስራት አጋጣሚ ነበረኝ። የአሰራትን እንቅስቃሴ እና አጨዋወት በጣም ነበር የምወደው። ከእሱም ብዙ ነገሮችን ተምሬያለው ብዬ ነው የማስበው።

ስለ መቐለ ከተማ ደጋፊዎች ምን ትላለህ ?  

በጣም ይገርምሀል እንዲህ በቃላት የምትገልፃቸው አይደሉም ። ለእኛ ብዙ ነገራችን ፣ 12ኛ ተጫዋቾች ናቸው ። ቡድኑም እዚህ ደረጃ የደረሰውም በእነርሱ ድጋፍ ነው። በምንጫወትበት ሜዳ እየመጡ ያበረታቱናል። በተለይ በሜዳችን መቐለ ላይ ስንጫወት ስታድየሙ ሞልቶ ነው እየደገፉን ያሉት። እኔ ለእነርሱ የምለው ቃላት የለኝም ፤ ለእኔም እዚህ መድረስ የእነርሱ አስተዋፆኦ ከፍተኛ በመሆኑ  በጣም ነው የምናመሰግናቸው ።

በመጨረሻ …

መጀመርያ እዚህ ደረጃ ያደረሰኝን ፈጣሪ ማመስገን እፈልጋለው። በመቀጠል እዚህ ደረጃ እንድደርስ ድጋፍ ላደረጉልኝ በሙሉ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *