ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅት ጀምሯል

በ2019 በኒጀር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የቶታል የአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ የመጀመርያ የማጣርያ ጨዋታውን ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታድየም ያደረገው የኢትዮዽያ ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቡሩንዲ 2 – 0 በሆነ ውጤት በመሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ እድሉን አጣብቂኝ ውስጥ መክተቱ ይታወሳል ። 

ቡድኑ ከጨዋታው በኋላ ለአንድ ሳሞንት እረፍት ተበትኖ የነበረ ሲሆን አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ለመልሱ ጨዋታ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን በማድረግ 18 ተጨዋቾችን ብቻ ይዘው በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ ከትላንት በስትያ ጀምሮ ዝግጅታቸውን እያደረጉ ይገኛል ።

ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር አብረው ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል ግብጠባቂው ፅዮን መርዕድ ፣ ተከላካዮቹ ዮናታን ፍስሀ እና ሰለሞን ወዴሳ ፣ አማካዮቹ ሚካኤል ሀሲሶ እና ሶፎንያስ መኮንን እንዲሁም አጥቂው ቃልኪዳን ዘላለም ከብሔራዊ ቡድኑ ውጭ ሲሆኑ ግብጠባቂው በረከት አማረ ከጉዳት መልስ ፣ ተከላካዩ ይትባረክ ሀብታሙ ( ከቡራዮ ከተማ ) እና አጥቂው እስራኤል እሸቱ ( ከሀዋሳ ከተማ ) ጥሪ ተደርጎላቸው ቡደሰኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ዛሬ ረፋድ ላይ ብሔራዊ ቡድኑ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሜዳ ከአይቮሪኮስት ከመጣ የፕሮጀክት ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርገዋል። አሰልጣኙ አጥናፉ አለሙም ዝግጅታቸውን በቀጣይ ቀናትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። ” የመጀመርያ ጨዋታ ላይ የነበሩብንን ድክመቶች በሚገባ አይተናል። በቀጣይ ድክመቶቻችንን አሻሽለን በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን ለመቀልበስ በቂ ዝግጅት እናደርጋለን ። በተወሰኑ ቦታዎች ላይ በነበሩን ክፍተቶች ላይ ተጫዋቾችን ቀንሰን በምትካቸው ሁለት ተጫዋቾችን ጨምረናል። ” ብለዋል።