ሪፖርት | መጨረሻው ባላማረው ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛው ሳምንት ሶዶ ላይ 1-1 ውጤት የተመዘገበበት የወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ በመልካም ሁኔታ ቢጀምርም በመጨረሻ ሰዐት በተነሳ ሁከት በአሳዛኝ ሁኔታ በድንጋይ ናዳ እና የአስለቃሽ ጭስ ታጅቦ እንዲጠናቀቅ ሆኗል፡፡

እለቱ የስራ ቀን የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሶዶ ስታድየም ከሌላው ጊዜ በተቀዛቀዘ መልኩ ቀስ በቀስ ሞልቶ እንደተለመደው የወላይታ ድቻ የደጋፊዎች ማህበር ለሀዋሳ ከተማዎች የእንኳን የደህና መጣችሁ ባነር አበርክተው እና የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ተዘምሮ ነበር የጀመረው።

ወላይታ ድቻዎች በያንግ አፍሪካንስ በተሸነፉበት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ከተጠቀሙበት የመጀመርያ 11 ተስፉ ኤልያስን በእሸቱ መና በማካተት በ4-3-2-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ሲገቡ ሀዋሳ ከተማዎች ደደቢትን ከረቱበት የ18ኛ ሳምንት ጨዋታ በጉዳት ያጡት ጅብሪል አህመድን በአስጨናቂ ሉቃስ ፣ ዳንኤል ደርቤን በመሳይ ጳውሎስ ተክተው በ4-2-3-1 አሰላለፍ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ስምንት ደቂቃን ከተያዘለት ሰአት ዘግይቶ በጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ሁለቱም ክለቦች ኃይል የተቀላቀለበት አጨዋወት ሲከተሉ ያስተዋልን ሲሆን ከሜዳው አመቺ አለመሆን ጋር ተጨምሮ የተጠበቀው እንቅስቃሴ እንዳይታይ አድርጓል። የመጀመሪያውን የግብ ዕድል ለመፍጠር ቀዳሚ የነበሩት የጦና ንቦች ነበሩ ፤ በ2ኛው ደቂቃ ላይ አምረላህ ደልታታ ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ውስጥ እየገፋ ገብቶ መሬት ለመሬት የመታት ኳስ ማንም ሳይደርስባት ወደ ውጪ ወጥታለች። 

ከዚህች ሙከራ በኋላ በ3ኛው ደቂቃ የሀዋሳ ከተማ የአማካይ ተጫዋቾች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ በዛብህ መለዮ ያሻገረውን ኳስ ሶሆሆ ሜንሳህ ለማዳን ሲወጣ ጃኮ አራፋት በላዩ ላይ አሳልፎ በቀድሞ ክለቡ ላይ በማስቆጠር ወላይታ ድቻን ቀዳሚ አድርጎል፡፡ ግቧ ስትቆጠር ጃኮ አራፋት ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ነበር በማለት ሀዋሳ ከተማዎች የእለቱ ረዳት ዳኛ ካሳሁን ፍፁምን ሲቃወሙ ተስተውሏል። ከዚህች ግብ በኋላ የድቻ ተጫዋቾች የኃይል አጨዋወት መጠቀማቸው ምክንያት ጨዋታው ውበቱን እንዲያጣ ሲያደርግ በሂደትም ሀዋሳ ከተማዎች በተመሳሳይ የኃይል አጨዋወትን ሲከተሉ ታይቷል። 15ኛው ደቂቃ ላይ በሀዋሳ በኩል ደስታ ዮሀንስ ከግራ መስመር የሰጠውን ኳስ እስራኤል እሸቱ ወደ ግብ ቢሞክርም ወንድወሰን ገረመው አምክኖበታል፡፡ ከዚህ በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች ኳስን ይዘው ለመጫወት ጥረት ማድረግ ሲጀምሩ ወላይታ ድቻዎች ረጃጅም ኳሶችን መሰረት ያደረገ አጨዋወትን ተከትለዋል። ቢሆንም በሜዳ ላይ የተጫዋቾች ጉሽሚያ በተለይ በሀዋሳው ፍሬው ሰለሞን እና በድቻው እሸቱ መና መካከል ያልተገቡ ድርጊቶችን በመፈፀማቸው ዳኛው ጨዋታውን አስቁሞ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው አልፏል። ጭማሪ ደቂቃ ላይ እስራኤል እሸቱ ለፍሬው ሰለሞን ሰጥቶት ፍሬው አክርሮ መቷት ወንድወሰን ገረመው የያዘበት ሙከራ የመጀመሪው አጋማሽ የመጨረሻ ሙከራ ነበረች።

ሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ እልህ አስጨራሽ የሆኑ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች የታዩበት እና ሁለቱም ቡድኖች በርካታ ያለቀላቸው ኳሶችን ያመከኑበት ነበር። ሆኖም የአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች በአሳዛኝ ሁኔታ የድንጋይ ውርጅብኝን ያስተናገዱ ነበሩ። እስከ ስልሳኛው ደቂቃ መባቻ ድረስ የግብ አጋጣሚዎችን ባንመለከትም በቀጣይ ግን ሀዋሳዎች አቻ ለመሆን ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸውል። በተለይ ታፈሰ ሰለሞን በሙሉአለም ረጋሳ ተቀይሮ ከገባ በኃላ ሀዋሳ ከተማ መሀል ሜዳ ላይ የተሻለ ብልጫን መውሰድ ችሏል። 60ኛው ደቂቃ ላይም በታፈሰ ሰለሞን ላይ በተሰራ ጥፋት በቀኝ የወላይታ ድቻ የግብ ክልል የተሰጠውን ቅጣት ምት ደስታ ዮሀንስ ሲያሻማት እስራኤል እሸቱ በግንባር ሞክሮ በወንደሰን ገረመው ሲመለስበት በአቅራቢያው የነበረው አስጨናቂ ሉቃስ በድጋሜ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ለማውጣት ጥረት ያደረገው እሸቱ መናን ጨርፋ ከመረብ አርፋለች። ሆኖም ኳሷ በእሸቱ መና ትጨረፍ እንጂ በአስጨናቂ ሉቃስ ስም መመዝገቧን አረጋግጠናል፡፡ 

68ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ወላይታ ድቻ በጃኮ አራፋት አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ ነው በማለት በረዳት ዳኛው ተሽራለች። 70ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳዊት ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ውብሸት ክፍሌ በደረቱ አብርዶ ወደ ግብ መቷት ሶሆሆ ሜንሳህ እንደምንም ይዞበታል፡፡ ሀዋሳዎች በብዙ የኳስ ንክኪ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ የጣሩበት ድቻዎች ደግሞ የመልሶ ማጥቃት አማራጭን በመጠቀም ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በፍጥነት ለመድረስ በሞከሩባቸው የመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ግብ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ አጋጣሚዎች የተመለከትን ሲሆን በዛው ልክ ደግሞ ድራማዊ እና ያልተገቡ ድርጊቶች እንዲሁም ጉዳቶች የትዕይንቱ አካሎች ነበሩ። 81ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ፍቃዱ ከታፈሰ ሰለሞን ያገኛትን ኳስ ከግብ ጠባቂው ወንደስን ጋር ተገናኝቶ ቢሞክርም ወደ ላይ ተነስቶበታል። የጨዋታውን መልክ የቀየረው ድርጊት የተፈፀመው ግን 86ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ወላይታ ድቻዎች በእዮብ አለማየሁ አማካኝነት ግብ ያስቆጥራሉ። ግቧ ከመቆጠሯ በፊት ሁለተኛ ረዳት ዳኛ የነበሩት ዳንኤል ግርማ ኳሷ ከጨዋታ ውጭ ነበረች በማለት አስቀድመው ማንሳታቸውን ተከትሎ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ደስታቸውን እየገለፁ ባለበት ሰአት በመጀመሪያው ውሳኔ መሰረት ግቧ ተሽራለች። ከዚህ ክስተት በኃላ የድቻ ደጋፊዎች የተለያዩ ቁሳቁሶችን ወደ ሜዳ በመወርወር በዳኞቹ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ሲያሰሙ ጨዋታው ለ12 ደቂቃዎች ያህል ለመቋረጥ ተገዷል፡፡

ሁኔታዎች በፀጥታ አካላት ከተረጋጉ በኃላ ወላይታ ድቻዎች ረዳት ዳኛው ዳንኤል ግርማ ላይ ክስ አስይዘው ጨወታው ቀጥሏል፡፡ አስራ ሁለት ደቂቃ የተቋረጠው ጨዋታ ሰባት ጭማሪ ደቂቃዎች ታክለውበት ቀጥሎ ከመጀመሪያዎቹ 80 ደቂቃዎች በተሻለ መልኩ ሁለቱም ቡድኖች ያለቀላቸውን አጋጣሚዎች አግኝተው ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። በጭማሪ ደቂቃ ላይ እዮብ አለማየሁ ለበዛብህ መለዮ አድርሶት በዛብህ የግብ ጠባቂው ሜንሳህን መውጣት አይቶ ወደ ግብ የመታትን ኳስ ጋናዊው ላውረንስ ላርቴ ከግቡ ጠርዝ ላይ እንደምንም አውጥቶበታል። አሁንም ኳሷ ስትመለስ በዛብህ መለዮ በድጋሚ ሲመታት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ዳግም አውጥቶበታል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ እስራኤል እሸቱ መጨረሻ ደቂቃ ላይ ያገኘውን ግልፅ የግብ ዕድል መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ ደግሞ ጃኮ አራፋት ከበዛብህ ያገኘውን ሌላ ኳስ እንዲሁ ወደ ግብ መቀየር ሳይችል ጨዋታው 1 ለ 1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ፡፡

ጨዋታው ከተጠናቀቀ እና ጋዜጠኞች የሁለቱን ቡድን አሰልጣኞች አሰተያየት ከተቀበሉ በኃላ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ዳግም ዳኛው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን በማሰማት ድንጋይ በሚወረውሩበት ወቅት ጉዳት አድርሰዋል። ይህን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ሁኔታውን ለማረጋጋት ያደረጉት ጥረት ከአንድ ሰዐት በላይ ወስዶ እና ጭሱ በስታድየሙ በነበሩ ተመልካቾች ላይ ጉዳት አድርሶ አመሻሽ ላይ ተረጋግቷል።