ሪፖርት | መቐለ ከመሪው ያለውን ልዩነት ያጠበበትን ወሳኝ ድል አስመዝግቧል 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት መርሃግብር ዛሬ መካሄድ ሲጀምር አዲስአበባ ስታዲየም ላይ መቐለ ከተማን ያስተናገደው ደደቢት ሽንፈት አስተናግዶ በወቅታዊ መጥፎ አቋሙ ገፍቶበታል፡፡

ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች በያዝነው ሳምንት አጋማሽ ወደ ጎንደር አቅንተው 1ለ0 ከተሸነፈው ስብስብ ምንም ቅያሪ ሳያደርጉ ተመሳሳይ ቡድን ይዘው ሲቀርቡ በአንጻሩ መቐለዎች በዛሬው ጨዋታ ላይ በቅጣት ያልተሰለፈው አንተነህ ገ/ክርስቶስን በዳንኤል አድሀኖም ብቻ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

እምብዛም ለተመልካች ሳቢ እንዲሁም በግብ ሙከራዎች ያልታጀበ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴን ማድረግ ችለዋል፡፡ በመከላከል ጥንካሬያቸው የሚታወቁት መቐለ ከተማዎች በተለይ በመጀመሪያ አጋማሽ ከአራቱ ተከላካይ ፊት የነበሩት ሁለቱ አማካዮች ማለትም ጋቶች ፓኖምና አመለ ሚልኪያስ እንቅስቃሴ ለደደቢት ሁነኛ የግብ አዳኝ ለሆነው ጌታነህ ከበደ ምንም አይነት የኳስ አቅርቦት እንዳይኖረው በማድረግ በኩል ውጤታማ ነበሩ። በጨዋታው በመቐለ በኩል በመጨረሻ አጥቂነት ጨዋታውን የጀመረው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከደደቢቱ የመሀል ተከላካይ ከሆነው ከድር ኩሊባሊ ደርስበት የነበረውን አካላዊ ጉሽሚያ ለመቋቋም ሲቸገር ተስተውሏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ከተደረጉት የግብ ሙከራዎች መሀከል በተለይ በ19ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በመቐለ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ የነበረው ጌታነህ ከበደ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የላካትን ኳስ የመቀለው ግብጠባቂ ኦቮኖ በድንቅ ሁኔታ አድኖበታል፡፡

በ25ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ ግብ ጠባቂ ክሌመንት አዞንቶ ለቡድን አጋሮቹ ለማቀበል ሲል የተሳሳተውን ኳስ ተጠቅሞ የመቐለው አምበል ሚካኤል ደስታ ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችውን ኳስ በቀላሉ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች ደደቢቶች በተሻለ ኳሱን በመቆጣጠር ወደፊት ለመሄድ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በ37ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው በደደቢት በኩል ያለወትሮው በመስመር አጥቂነት ሲጫወት የነበረው ሰለሞን ሀብቴ ከመቐለ የግብ ክልል ግራ ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታትና ፌሊፕ ኦቮኖ ያዳነበት ኳስ ውጪ ተጠቃሽ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡

በጨዋታው 43ኛው ደቂቃ ላይ ሁለቱ የደደቢት የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተሰላፊዎች የሆኑት ከድር ኩሊባሊና ደስታ ደሙ በአየር ላይ ኳስ ከመቀለው አጥቂ ከሆነው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ጋር ተሻምተው ለመግጨት ሲሉ እርስ በርሳቸው በመላተማቸው ደስታ ደሙ ሜዳ ውስጥ ራሱን በመሳቱ ለ5 ያክል ደቂቃዎች ጨዋታው ተቋርጦ የህክምና እርዳታ ተደርጎለት ከሜዳ በፋሲካ አስፋው ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ በ4 አጋጣሚዎች ሁለቱ በመስመር አጥቂዎች ሰለሞን ሀብቴና ኤፍሬም አሻሞ ቦታቸውን የተቀያየሩ ቢሆንም ይህም በጨዋታው ሂደት ላይ የፈጠረው ይህ ነው የሚባል ተፅዕኖ አልነበረም ብሎ ለመናገር ያስደፍራል፡፡ በአንጻሩ በመቐለዎች በኩል የመጀመሪያዋን ግብ ካስቆጠሩ በኃላ አምበላቸውን ሚካኤል ደስታን ወደ ኃላ በመመለስ ከአመለ ጋር በመሆን በ4-2-3-1 አሰላለፍ ከአራቱ ተከላካዮቹ ፊት እንዲጫወት አድርገዋል ፤ በዚህም ቅያሪ በቀደሙት ደቂቃዎች የአመለ አጣማሪ የነበረው ጋቶች ፓኖም ወደ 10 ቁጥር ሚና እንዲመጣ አስችሎት ነበር። ይህ ለውጥ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ጋቶች ፓኖምና አጥቂው አማኑኤል ገ/ሚካኤል በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ጊዜ የነበራቸው ተግባቦት እጅግ የሚያስደንቅ ነበር፡፡ በተለይም ጋቶች ፓኖም በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በደደቢት ተከላካዮች መሀል ያሳለፈለትን ሰንጣቂ ኳስ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ሳይጠቀምባት ቀረ እንጂ ለዚህ ተግባቦት ጥሩ ማሳያ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በተለይ ደደቢቶች በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቆየት በሙሉ ሃይላቸው አጥቅተው ለመጫወት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ነገርግን የመቀለ ከተማ የመከላከል አደረጃጀት ግን የሚቀመስ አልሆነም፡፡ በርካታ ተጫዋቾች በማጥቃት ወረዳ ውስጥ በማስገባት የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር ሲሞክሩ የነበሩት ደደቢቶች በ56ኛውና በ72ኛው ደቂቃ ከቆመ ኳስና በጨዋታ ጌታነህ ከበደ ከሞከራቸው ኳሶች በዘለለ ተጠቃሽ ሙከራዎችን ማድረግ አልቻሉም፡፡

በአንጻሩ ከመጀመሪያው በተሻለ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ተነሳሽነት ያሳዩት መቀለዎች በተለይም በ59ኛው ደቂቃ ላይ ፎሲይኒ ከመስመር ያሳለፈለትና ቢስማርክ ተንሸራቶ ለጥቂት ሳይደርስባት የቀረው እንዲሁም በ63ኛው ደቂቃ የደደቢት ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል በተዘናጉበት ቅፅበት ፎሲይኒ ለአማኑኤል ያሳለፈለትን ኳስ አማኑኤል ከደደቢቱ ግብጠባቂ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ያመከናት ኳስ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ለመጠቀም በመሞከሩ ረገድ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ ስለመሆናቸው በራሱ ይናገራሉ፡፡ በ86ኛው ደቂቃ ላይ የመቐለው አጥቂ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ላይ ከድር ኩሊባሊ በሰራው ጥፋት መቐለዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት አማኑኤል ገ/ሚካኤል አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። አማኑኤል ላይ ጥፋት የፈፀመው ከድር ኩሊባሊም በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ከሁለተኛዋ ግብ መቆጠር በኃላ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ደደቢቶች ያገኙትን የቅጣት ምት ስዩም ተስፋዬ ያሻማውን አስራት መገርሳ በግንባሩ በመግጨት ደደቢቶችን ከባዶ መሸነፍ ያዳነችውን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በመቐለ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቀል።

ውጤቱን ተከትሎ መቐለ ከተማ ከመሪው ጅማ አባጅፋር ጋር ያለውን ልዩነት ወደ 3 በማጥበብ በ32 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ደደቢት አሁንም በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት 

ጌቱ ተሾመ – ደደቢት

በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ በጨዋታ ብልጫ እየወሰድን ማሸነፍ ሳንችል ቀርተናል ፤ የዛሬውን ጨዋታ ግን እኔ ተሸነፍን ብዬ ለመቀበል እቸገራለሁ፡፡ የሚገባንን የፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል ፤ በተቃራኒው የማያሰጥ የፍፁም ቅጣት ተሰቶብናል። ይባስ ብሎ ተጫዋች በቀይ ወቶብናል፡፡ ነገርግን አሰልጣኝ ዳኛ ላይ አስተያየት ሰጠ ተብሎ የሚቀጣበት ጊዜ ላይ ስለደረስን በዳኝነቱ ላይ ከዚህ በላይ  አስተያየት መስጠት አልችልም፡፡ አሰልጣኞችን የሚቀጡትን አካላት የሚቀጣው አካል ባይታወቅም ተጫዋቾቻችን ዘጠና ደቂቃ የተቻላቸውን አድርገዋል። ነገርግን ተሸንፈናል፡፡

ዮሀንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ

በጨዋታው የተሻልን ስለነበርን ማሸነፋችን ይገባናል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻልን የነበርን ቢሆንም ብዙም ወደግብ መድረስ አልቻልንም ነበር። የሆነው ሆኖ ግብ ማስቆጠር ችለናል ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ግን ከመጀመሪያው በተሻለ በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስ ችለን ብዙ ኳሶችን አበላሽተናል፡፡