ሪፖርት | ወላይታ ድቻ በእዮብ አለማየሁ ሐት-ትሪክ ታግዞ ፋሲልን አሸንፏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት መርሃግብር ሁለት ጨዋታዎችን ከሜዳው 150 ኪሜ ርቀት ላይ እንዲያደርግ ቅጣት የተላለፈበት ወላይታ ድቻ ሰበታ ላይ ፋሲል ከተማን አስተናግዶ በወጣቱ እዮብ አለማየሁ ሐት-ትሪክ ታግዞ 3-0 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል። 

ፋሲል ከተማ ጎንደር ላይ ደደቢትን ከረታው የመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ በግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ከቅጣት የተመለሰው አምሳሉ ጥላሁንን በፍፁም ከበደ ምትክ ወደ ሜዳ ሲያስገባ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪም የቀድሞ ክለባቸውን ለመጀመርያ ጊዜ በተቃራኒው ገጥመዋል። በወላይታ ድቻ በኩል በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጨረሻ ጨዋታ ያንግ አፍሪካንስን 1-0 ካሸነፈው ቡድኑ ውስጥ ዘላለም እያሱ እና ያሬድ ዳዊትን አሳርፎ አምረላ ደልታታ እና ፀጋዬ ባልቻን የመጀመሪያ አሰላለፍ ዕድል ሰጥቷቸዋል።

ለ20 ደቂቃዋች ዘግይቶ የጀመረው ይህ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ታይቶበታል። የመጀመሪያዎቹን 20 ደቂቃዎች በእንቅስቃሴም ሆነ ወደግብ በመድረስ የተሻሉ የነበሩት ፋሲል ከተማዎች በ1ኛው ደቂቃ ፊሊፕ ዳውዝ በግንባሩ በመግጨት ባደረገው ሙከራ የመጀመሪያውን አጋጣሚ ሲፈጥሩ በ9ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ ኃይሉ በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ መሬት ለመሬት አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ገረመው ወደ ውጪ አውጥቶበታል። በ17ኛው ደቂቃ ላይ ያስር ሙገርዋ በግምት 18ሜትር ርቀት ላይ የመታት ኳስም የግቡን አግዳሚ ታካ ወጥታበታለች።  በተቃራኒው ወላይታ ድቻ የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ በጃኮ አረፋት አማካይነት ካደረገ ከአንድ ደቂቃ በኋላ በ20ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ ያሻማውን ኳስ እዮብ አለማየሁ ወደግብነት ለውጦ የጦና ንቦችን መሪ ማድረግ ችሏል። 

ከጎሉ በኋላ በሁለቱም በኩል የጎል ሙከራዎች የታዩ ሲሆን በፋሲል በኩል በ25ኛው ደቂቃ አምሳሉ ጥላሁን ያሻማውን ኳስ ፊሊፕ በግንባሩ ገጭቶ በተከላካይ ተድርቦ የወጣበት እና በ29ኛው ደቂቃ ላይ ኤርምያስ ኃይሉ ከያስር  ያገኘውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጊዜ ሳይጠብቅ በመውጣቱ ያለፈውን ኳስ ወደ ግብ መትቶ ተክሉ ታፈሰ ያዳነበት ፣ በወላየታ ድቻ በኩል ደግሞ በ28ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ባልቻ ያሻማውን ኳስ እዮብ በፍጥነት አክርሮ መትቶ የግቡን አግዳሚ ጨርፎ የወጣበት እና በ33ኛው ደቂቃ በዛብህ ያሻገረትን ኳስ ጃኮ ተንሸራቱ መትቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት ተጠቃሾች ነበሩ። 

በ42ኛው ደቂቃ አብዱልሰመድ ዓሊ ወደ ፊት ያሻገረውን ኳስ በዛብህ መለዮ በመቆጣጠር የፋሲል ከተማ ግብ ጠባቂ መውጣት ተመልክቶ በግብ ጠባቂው አናት በማሳለፍ ለእዮብ ያቀበለውን ኳስ ወጣቱ አማካይ እዮብ አለማየሁ በአግባቡ በመጠቀም ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሮ የመጀመርያው አጋማሽ በወላይታ ድቻ መሪነት ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ሙሉ ለሙሉ ፋሲል ከተማዋች ተጭነው መጫወት የቻሉ ቢሆንም ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። በ50 ደቂቃ ያስር ከርቀት የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ጥረት ወደውጪ የወጣበት ፣ በ54ኛው ደቂቃ ያስር በድጋሚ ግብ ጠባቂውን አልፎ የመታው ኳስ ተስፋ ኤልያስ ደርሶ ያዳነበት ፣ በ60ኛው ደቂቃ ራምኬል ሎክ ገጭቶ ወንድወሰን ያወጣበት ፣  በ71ኛው ደቂቃ ኄኖክ ገምቴሳ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት መከራዎች ጫና ለመፍጠራቸው ማሳያ ነበሩ። በ78ኛው ደቂቃ በድቻ ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመነካቱ ፋሲሎች የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኙም ከድር ኸይዲን የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን አድኖበታል። 

በጨዋታው ያገኟቸውን እድሎች በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ስኬታማ የነበሩት ድቻዎች በመገባደጃ ደቂቃዎች ድላቸውን ይበልጥ ያረጋገጡበትን ጎል አስቆጥረዋል። በ88ኛው ደቂቃ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ እዮብ አለማየሁ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በወላይታ ድቻ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ወላይታ ድቻ ነጥቡን 27 በማድረስ 9ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ከተከታታይ ሁለት ድሎች በኋላ የተሸነፈው ፋሲል በ32 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።