አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋን በክለቡ ያቆየው ሀዋሳ ከነማ 7 ተጫዋቾችን ማስፈረሙን ዛሚ ስፖርት ብሄራዊ ዘግቧል፡፡ ሀዋሳ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ግብ ጠባቂው ዮሃንስ በዛብህን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ የአጥቂ አማካዩ ገዛኸኝ ወልዴን ከሐረር ሲቲ ፣ አማካዩ መስፍን ዳምጠው (ሚጣ) ከልደታው ኒያላ ፣ አጥቂው ገብረሚካኤል ያእቆብን ከአርባምንጭ ከነማ ፣ አግላን ቃሲም እና ሙጂብ ቃሲምን ከሲዳማ ቡና እንዲሁም የሙገሩን ግብ ጠባቂ ብርሃኑ በላይ ናቸው፡፡
የደቡቡ ክለብ ግብ ጠባቂው ቢንያም ሐብታሙን የለቀቀ ሲሆን በምትኩ ሁለት ግብ ጠባቂዎችን አስፈርሟል፡፡ በተለይም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በንግድ ባንክ ድንቅ የውድድር ዘመን ያሳለፈው ዮሃንስ ግዢ በምርጥነቱ ይጠቀሳል፡፡
ሌላው ክለቡን የለቀቀው አንዱአለም ንጉሴ (አቤጋ)ን ቦታ በፕሪሚር ሊጉ ጥሩ ከሚባሉ አጥቂዎች መካከል አንዱ በሆነው ገብረ ሚካኤል ያእቆብ ሸፍነውታል፡፡ ‹‹ አቱማ በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው የቀድሞው የሲዳማ ቡና አጥቂ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ጥሩ አቋም ማበርከት ባይችልም በብሄራዊ ቡድኑ እና በክለቡ ላለፉት አመታት ምርጥነቱን ያስመሰከረ አጥቂ ነው፡፡
ዘንድሮ ከፕሪሚየር ሊጉ በወረደው ሐረር ሲቲ ውስጥ ሊጠቀስ የሚችል ድንቅ አቋም ያሳየው የቀድሞው የደደቢት ፣ መድን እና ሰበታ ከነማ አማካይ ገዛኸኝ እንዳለ ሀዋሳን ለቆ ለመብራት ኃይል ፈረመው ወንድሜነህ ዘሪሁንን ቦታ ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አግላን በአጥቂ ፣ ሙጂብ በተከላካይ መስመር ድንቅ የውድድር ዘመን ሳለፉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የቀድሞው የንግድ ባንክ እና ኢትዮጵያ ቡና አማካይ መስፍን ዳምጠው ደግሞ በክህሎት እና ልምድ የበለፀገ ተጫዋች ነው፡፡ ዘንድሮ በወጣቱ አሰግድ አክሊሉ ቦታውን የተነጠቀው ግብ ጠባቂው ብርሃኑም የዮሃንስ ተጠባባቂ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡