ሪቻርድ አፒያ ወደ ሀገሩ አቅንቷል

በጉዳት ለ7 ወራት እንደሚርቅ በክለቡ የተረጋገጠው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዲስ ፈራሚ ሪቻርድ አፒያ ለህክምና ወደ ሀገሩ አቅንቷል።

ጋናዊው አጥቂ ለክለቡ የፈረመው በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ ሲሆን ከተገቢነት ጋር በተያያዘ ፊርማው ውድቅ ተደርጎ ኋላ ላይ ክለቡ ባቀረበው ይግባኝ መሠረት ተፈቅዶለት ለፈረሰኞቹ መጫወት መጀመሩ የሚታወስ ነው። ቡድኑ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ተቀይሮ በመግባት ለመጀመርያ ጊዜ የተጫወተ ሲሆን ኤሌክትሪከን በገጠሙበት ጨዋታ በመጀመርያ አሰላለፍ ተካቶ ጎል ማስቆጠር ቢችልም በጉዳት ተቀይሮ ወጥቷል።

ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ያመለጡት ሪቻርድ አፒያ ከጉልበት ጉዳቱ በፍጥነት ለማገገም በማሰብ ከትናንት በስቲያ ወደ ሀገሩ ጋና ማቅናቱ የተሰማ ሲሆን መቼ ህክምናውን አጠናቆ ከክለቡ ጋር እንደሚቀላቀል አልታወቀም።

በዘንድሮ ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ በጉዳት እየታመሰ ይገኛል። በተለያዩ ወቅቶች በርካታ ተጫዋቾች ሲጎዱ በአሁኑ ወቅትም ታደለ መንገሻ ፣ ሳላዲን ሰዒድ እና በሁለተኛው ዙር ክለቡን የተቀላቀለው አማራ ማሌ በጉልበት ጉዳት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።