የቢኒያም አሰፋ አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቷል

በኢትዮ ኤሌትሪክ እና በቢኒያም አሰፋ መካከከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ተጨዋቹ ባቀረበው ቅሬታ ዙርያ የዲሲፒሊን ኮሚቴው ውሳኔ ሰጥቷል።

በውድድር አመቱ መጀመርያ ለኢትዮ ኤሌትሪክ ፊርማውን ያኖረው አንጋፋው አጥቂ ቢኒያም አሰፋ በአዲሱ ክለቡ የተረጋጋ ጊዜ ሳያሳልፍ በጥቂት ጨዋታዎች ብቻ በመሰለፍ በመጨረሻም ከየካቲት 27 ጀምሮ ከስራው መሰናበቱ የሚታወስ ነው። ይህን ተከትሎም ተጨዋቹ ‘ያለአግባብ ከስራ ተሰናብቻለው’ በማለት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቤቱታውን አቅርቧል። በአቤቱታውም መሰረት ፌዴሬሽኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጉዳዩ ላይ መልስ እንዲሰጥ በጠየቀው መሰረት ክለቡ ተጨዋቹ የልምምድ ፕሮግራም አያከብርም ፣ ልምምድ አይጨርስም ሌሎችም እንዳይሰሩ ያደርጋል ፣ በተጨዋቾች ፊት አሰልጣኙን ተሳድቧል በሚሉ እና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ሁለቴ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ከሰጠው በኃላ እንዳሰናበተው ገልጿል።

ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የዲሲፒሊን ኮሚቴም በክለቡ እና በተጨዋቹ መሀከል የተፈረመውን ውል አንቀፅ 4 በመጥቀስ እና የክለቡ ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑን በማመን የተጨዋቹ ስንብት እንዲሻር ፣ ኢትዮ ኤሌትሪክ ተጨዋቹን ወደ ስራ እንዲመልስ እና የግልግል ጉባዔ በማቋቋም ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እስከዛው ድረስ ግን ክለቡ ለተጨዋቹ ደሞዝ እንዲከፍለው ውሳኔ አሳልፏል። ከዚህ በተጨማሪም ክለቡ ውሳኔውን በተግባር የማይፈፅም ከሆነ ከውድድር እንዲታገድ እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ምንም አይነት ግልጋሎት እንዳያገኝ ጨምሮ ወስኗል።