ለአሰልጣኝ ሥዩም አባተ ህክምና የገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታ ይደረጋል

የአሰልጣኝ ሥዩም አባተን ጤና ለመመለስ እሁድ በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚገናኙበት የገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታ ይደረጋል።

ያለፈውን አንድ አመት በህመም ላይ የሚገኙት አንጋፋው አሰልጣኝ ሥዩም አባተ ወደ ጤንነታቸው እንዲመለሱ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። እስካሁን ድረስ በተሰበሰበው ገንዘብም አሰልጣኙ ለተሻለ ህክምና ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ታይላንድ ባንኮክ አቅንተው ህክምናቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። አሰልጣኙ ሙሉ ለሙሉ ከህመማቸው አገግመው በጤና ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ እና ጥሩ የህክምና ክትትል እንዲደረግላቸው አሁንም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ይህን ገንዘብ ለማግኘት ኮሚቴው ስራውን አጠናክሮ ቀጥሏል። የዚህ ጥረት አንድ አካል በሆነው የገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታም የፊታችን እሁድ ግንቦት 26 10:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጽያ ቡናን ከኢትዮ ኤሌትሪክ የሚያገናኘው ጨዋታ እንደሚከናወን ተገልጿል።

በዚህም መሰረት የታላቁን የእግር ኳስ ሰው ህይወት ለመታደግ የስፖርት ቤተሰቡ በዕለቱ በአዲስ አበባ ስታድየም በመታደም የተለመደውን ድጋፍ እንዲያደርግ ኮሚቴው ጥሪውን አስተላልፏል።