ሀዋሳ ከተማ ልምምድ አቁሟል

የፕሪምየር ሊጉ ክለብ ሀዋሳ ከተማ በየእለቱ የሚያከናውነው መደበኛ የልምምድ መርሐ ግብር መቋረጡ ተገለፀ።

ሊጠናቀቅ ጥቂት ጨዋታዎች በሚቀረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና በ25ኛው ሳምንት ተጫውተው 1-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ ላይ የሲዳማ ቡናው አዲስ ግደይ የተገቢነት ክስ ቀርቦበት ፌድሬሽኑ ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በ24ኛው ሳምንት አዳማን የረታበት ጨዋታን ለአዳማ ከተማ ሶስት ነጥብ እና ሶስት ግብ መሰጠቱ ይታወሳል። 

ይህን ተከትሎ አንዳንድ ግለሰቦች ይህን ድርጊት ሆን ተብሎ ክለቡ እንዲቀጣ ያደረጉት ነው በሚል የሀዋሳ ከተማ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ም/አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት አንዲሁም ቡድን መሪው አለምባንተ ማሞ ላይ ጥቃት ለማድረስ ዛቻዎች እየደረሷቸው በመሆኑ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ማቅናታቸው ተነግሯል። ሆኖም ክለቡ በግብ ጠባቂው አሰልጣኝ አምጣቸው ኃይሌ እየተመራ ከኤሌክትሪክ ጨዋታ መልስ ልምምድን ሲሰራ የቆየ ቢሆንም በከተማዋ በነበረው የጸጥታ ችግር እና አሰልጣኞቹ በስራ ገበታቸው ላይ ካለመገኘታቸው ጋር በተያያዘ ከሐሙስ ጀምሮ ያለፉትን አራት ቀናት ልምምድ እንዳቆመ ታውቋል፡፡

የክለቡ አሰልጣኞች እስካሁን ወደ ሀዋሳ ያልተመለሱ ሲሆን ክለቡ ልምምድ ማቆሙን ተከትሎ ቀጣዩ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታን የማድረጉ ሁኔታ አጠራጥሯል። የክለቡ ከ17 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች ቡድንም በዚህ ሳምንት ጨዋታ አለማድረጉ ይታወሳል።