የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በዚህ ሳምንት

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ (23ኛ ሳምንት) እና የምድብ ለ (22ኛ እና 23ኛ ሳምንት) ጨዋታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ከቅዳሜ ጀምሮ እስከዛሬ ተካሂደዋል። 

ምድብ ሀ

ቅዳሜ በኦሜድላ ሜዳ የካ ከነቀምት ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ በርካታ እንግዳ ክስተቶችን አስተናግዶ አልፏል። አወዛጋቢ በነበረው በመጀመሪያው አጋማሽ በ5ኛው ደቂቃ ላይ የካ ክፍለ ከተማ በሐብታሙ ከበደ አማካኝነት ወደ ግብ አክርሮ በመምታት የመጀመርያውን ሙከራ አድርገዋል። በ17ኛው ደቂቃ የነቀምት ተጫዋች በየካው ምናልካቸው ላይ ከኳስ ውጪ ጥፋት በመስራቱ የዕለቱ ዳኛ የቀይ ካርድ ማሰየታቸውን ተከትሎ ከነቀምት የአሰልጣኞች መቀመጫ ከፍተኛ ተቃውሞ በዕለቱ ዳኛ ላይ አሰምተዋል። ከ9ደቂቃ በኋላ ሐብታሙ ከበደ ላይ ከጨዋታ ውጭ በተሰራው ጥፋት ተጫዋቹ ላይ ከፍተኛ ጎዳት በመድረሱ በዕለቱ በነበረው የጠብታ አምቡላንስ የመጀመርያ እርዳታ በላይ በመሆኑ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ጦር ኃይሎች እንዲያመራ ተደርጓል። ጨዋታውም ለ18 ደቂቃዋች ከተቋረጠ በኋላ ሲጀምር ያለምንም የማስጠንቀቂያ ካርድ በመታለፉ የካዎች ቅሬታቸውን ገልፀዋል።

በ28ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የነቀምት ከተማው አሰልጣኝ ቾንቤ ገ/ህይወት በቀይ ካርድ ከአሰልጣኝ መቀመጫቸው እነረዲነሱ ተደርጓል። ከዕረፍት መልስ የካ ክፍለ ከተማዎች ጫና መፍጠር ቢችሉም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ቅዳሜ በተደረጉ ሌሎች ጨዋታ ኢኮስኮ በዓባይነህ ፋኖ እና የኋላሸት ፍቃዱ ጎሎች ወሎ ኮምቦልቻን 2-0 አሸንፏል።

እሁድ ሱሉልታ ላይ ሱሉልታ ከተማን የገጠመው ባህርዳር ከተማ 3-1 በማሸነፍ መሪነቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ጨዋታ በ17ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ውዱ በግንባሩ አስቆጥሮ ባህር ዳር መሪ መሆን ቢችልም በ30ኛው ደቂቃ ከርቀት ሲሳይ አማረ አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ግብነት ተለውጦ በአቻ ውጤት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል። በ48ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ሙሉቀን አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሲመልሰው በአቅራቢያው የነበረው ፍቃዱ ወርቁ ወደግብነት ለውጦ ባህር ዳርን መሪ ማድረግ ሲችል በ55ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን ታሪኩ ለባህርዳር በግሩም አጨራረስ ሶስተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በባህርዳር 3-1 አሸንፏል።

መድን ሜዳ ላይ አዲስ አበባ ከተማ ፌደራል ፖሊስን ገጥሞ 5-0 ማሸነፍ ችሏል። ፍቃዱ ዓለሙ እና ድንቅነህ ከበደ ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥሩ ጌታነህ ሙሉነህ የቀሪዋ ጎል ባለቤት ነው። በጨዋታው ፌዴራል ፖሊሶች በአአ ከተማ ላይ የተጫዋች ተገቢነት (5 ቢጫ) ክስ አስመዝግበዋል። ሽረ ላይ ቡራዩ ከተማን የገጠመው ሽረ እንዳሥላሴ 1-0 በመብራህቶም ፍስሀ ጎል 1-0 ሲያሸንፍ ሰበታ ከተማ በዐብይ ቡልቲ ብቸኛ ጎል አክሱም ከተማን በተመሳሳይ 1-0 አሸንፏል። ኢትዮጵያ መድን ከ ለገጣፎ ለገዳዲ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሲለያዩ ከቅዳሜ ወደ ዛሬ የተሸጋገረው የአውስኮድ እና ደሴ ከተማ ጨዋታም በተመሳሳይ 1-1 ተጠናቋል።

ምድብ ለ 

ቅዳሜ መሪው ደቡብ ፖሊስ ሻሸመኔ ከተማን 4-0 በማሸነፍ በመሪነቱ ቀጥሏል። ድንቅ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ብሩክ ኤልያስ ሶስት ጎሎች አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ ሲሰራ በኃይሉ ወገኔ የቀሪዋ ጎል ባለቤት ነው። ቅዳሜ ተጀምሮ በዝናብ ምክንያት በመቋረጡ በቀጣዩ ቀን በተጠናቀቀ ጨዋታ ዲላ ከተማ ቤንች ማጂ ቡናን በኄኖክ አየለ ጎል 1-0 ሲረታ ወደ ወራቤ ያመራው ጅማ አባ ቡና በብዙዓየሁ እንደሻው እና ኃይለየሱስ ብርሀኑ ጎሎች 2-1 አሸንፎ መመለስ ችሏል።

እሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች ቡታጅራ ከተማ በኤፍሬም ቶማስ ሁለት ጎሎች ታግዞ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 ሲረታ ሀምበሪቾ በቴዲ ታደሰ ብቸኛ ጎል ድሬዳዋ ፖሊስን 1-0 አሸንፏል። ወደ መቂ ያመራው ወልቂጤ ከተማ ደግሞ 1-0 አሸንፏል።

በምድብ ለ ቅዳሜ እለት ብቸኛ የ23ኛ ሳምንት ጨዋታ በናሽናል ሴሜንት እና ነገሌ ከተማ መካከል ተካሂዶ ያለ ግብ ተጠናቋል። በዚህ ጨዋታ ምክንያትም ነገሌ ከተማ ከ ሀላባ ከተማ ሊያደርጉት የነበረው የ22ኛ ሳምንት መደበኛ መርሀ ግብር ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።