የአሴጋ እግርኳስ አካዳሚ ዛሬ ምሽት ወደ ስዊድን አምርቷል

በዓለማችን ካሉ የታዳጊዎች የእግርኳስ ውድድር ውስጥ ብዙ ቡድኖችን በማሳተፍ ቀዳሚ የሆነው የጎቲያ ዋንጫ ሰኞ በጎተንበርግ ስዊድን ይጀምራል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍም የአሴጋ እግርኳስ አካዳሚ ዛሬ ምሽት ወደ ስፍራው አቅንቷል፡፡ አሴጋ የተቋቋመው አሁን በህይወት በሌለው የቀድሞ ድንቅ አጥቂ አሰግድ ተስፋዬ መሆን ይታወቃል፡፡

አሴጋ የዘንድሮውን ጨምሮ ለሶስት ጊዜያት ያህል በዓለምአቀፍ የታዳጊ ዋንጫ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ችሏል፡፡ አካዳሚው በጎቲያ ዋንጫው ላይ ከ18 ዓመት በታች ውድድር ላይ የሚሳተፍ ሲሆን 18 ተጨዋቾች እና ሶስት የአሰልጣኝ አባላትን የያዘው ስብስቡ ዛሬ ምሽት ስዊድን ያመራል፡፡ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቿ ራውዳ አሊ፣ ኃይሉ አድማሱ (ቻይና) እና ዐብይ ካሳሁን በአሰልጣኝነት ቡድኑን እየመሩት ይገኛሉ፡፡

የቡድኑ አሰልጣኝ የሆነው ዐብይ ካሳሁን ስለአሴጋ እግርኳስ አካዳሚ ከሃገር ውጪ ውድድሮች ላይ ያለውን ተሳትፎ በሚመለከት ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ “በመጀመሪያ ተሳትፏችን ከ16 እና ከ15 ዓመት በታች ሁለት ቡድን ነበር ይዘን የቀረብነው፡፡ አምና ከ16 ዓመት በታች ቡድን ይዘን ነበር የተጫወትነው፡፡ በአሁኑ ደግሞ ከ18 ዓመት ነው ይዘን የቀረብነው፡፡”

ቻይና ላይ በተደረገ ከ18 ዓመት በታች ውድድር ላይ ቻምፒዮን የሆነው አካዳሚው በዚኛው ስብስብ ላይም ከዓምናው ስብስብ የተካተቱ ተጨዋቾች እንዳሉ አሰልጣኝ ዐብይ ጠቁመዋል፡፡ “አምና ቻይና ላይ ከተሳተፈው የ18 ዓመት በታች እና ስዊድን ላይ ከተሳተፈው የ16 ዓመት በታች ቡድናችን መካከል ተጨዋቾችን አካተናል፡፡ ሌላ በውሰት የምንወስዳቸው አሉ፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን ሁለት ልጆች አሉ፡፡ ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ ደግሞ የኛው ልጅ የሆነ አንድ ተጨዋች አለ፡፡”

የዓመለ ሸጋው አሰግድ ተስፋዬ ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ አካዳሚው በ2009 መጨረሻ ላይ በሁለት ሃገራት ውድድሮችን ያካሄደ ሲሆን በያዝነው አመት በተለይ ከመጫወቻ ሜዳ ጋር ተያይዞ ችግሮች ተፈጥረው እንደነበር አሰልጣኝ አብይ አስረድተዋል፡፡ “አሴ ከሞተ በኃላ ነው ስዊድንም ቻይናም የሄድነው፡፡ ግን አሴ ነው ሁሉንም ነገር ያስተካከለው፡፡ ከቻይና መልስ ወጣቶች አካዳሚ ነበር የምንሰራው ያው ውጡ አሉን፡፡ እሁድ እሁድ ፕሮግራም ሰጥተውን ተባብረውን ነበር የምንሰራው አሰግድ እያለ፡፡ አሁን ሌላ ሜዳ ተከራይተን መስራት አለብን ብለን 22 ሜዳ ስራ ጀመርን፡፡”

ቡድኑ ዛሬ ምሽት ወደ ስዊድን ከማቅናቱ ቀደም ብሎ አሰግድን ለማሰብ ስሙ እና ምስሉ የታተመበትን ቲ-ሸርት በማድረግ የቀድሞ የኢትዮጵያ መድን፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ብሄራዊ ቡድን የፊት መስመር ተሰላፊ እንደሚያስብ አሰልጣኝ ዐብይ ጨምረው ገልፀውልናል፡፡

ጎቲያ ዋንጫ በስዊድኑ ክለብ ቢኬ ሃከን አዘጋጅነት መደረግ ከጀመረ ከአርባ አመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ቢኬ ሃከን የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመሃል ተከላካይ ዋሊድ አታ ክለብ ነው፡፡ በውድድሩ ላይ ከ1700 በላይ የታዳጊ ቡድኖች በተለያዩ የእድሜ እርከኖች ተከፋፍለው ይጫወታሉ፡፡ አሴጋ የእግርኳስ አካዳሚም በውድድሩ ላይ በምድብ ሁለት በኖርዌው ቦስኮፕ፣ ከጀርመኑ ቫልዶርፈር እና ከስዊድኑ ቢኬ ፎርዋርድ ጋር ተደልድሏል፡፡

የአሴጋ እግርኳስ አካዳሚ የጨዋታ ቀኖች

ሰኞ ነሃሴ 9/2010

አሴጋ የእግርኳስ አካዳሚ ከ ቫልዶርፈር

ማክሰኞ ነሃሴ 10/2010

ቦስኮፕ ከ አሴጋ የእግርኳስ አካዳሚ

ዕረቡ ነሃሴ 11/2010

ቢኬ ፎርዋርድ 1 ከ አሴጋ እግርኳስ አካዳሚ