ሪፖርት | የወልዋሎ እና ድሬዳዋ ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ተቋርጦ ወደ ነገ ተላልፏል

ዓዲግራት ላይ ድሬዳዋን ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያገናኘው ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት ዘልቆ በሁለተኛው አጋማሽ በከባድ ዝናብ ምክንያት ተቋርጧል። ነገ ረፋድ ይቀጥላል ተብሎም ይጠበቃል። 

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ወልዋሎ በሊጉ መቆየቱን ምክንያት በማድረግ በክለቡ ደጋፊዎች የተዘጋጀው አጠር ያለ ፕሮግራም ተካሂዶ ጨዋታው የተጀመረ ሲሆን መጀመርያ አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች የተከላካይ ክፍላቸውን ወደ መሃል ሜዳ በማስጠጋት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለማግኘት ቢጥሩም በነበረው እጅግ የተጠጋጋ የተጨዋቾች ቦታ አያያዝ ምክንያት ሜዳው ተጨናንቆ አንዳቸውም በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል መድረስ አልቻሉም።

4-4-2 አደራደርን ምርጫቸው አድርገው የገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በበርካታ አጋጣሚዎች ኳስን መስርተው ለመውጣት ቢሞክሩም መሃል ሜዳ ላይ በወልዋሎ የመሃል ሜዳ ተጫዋቾች የተወሰደባቸውን የቁጥር ብልጫ ቀጣይነት እንዳይኖረው እና ከቀላል የጎንዮሽ ቅብብል ያለፈ እንዳይሆን አድርጎታል። ከዚ በፊት በተመሳሳይ ተጫዋቾች የተገነባና የፈጣሪነት ውስንነት የነበረው የወልዋሎ መሃል ሜዳ ክፍል በዚህ ጨዋታ የፈጠራ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾችን ይዞ በመግባቱ ከድሬዳዋ በተሻለ ብዙ የጎል እድሎች እንዲፈጥር አስችሎታል። እንየው ካሳሁን በጥሩ ሁኔታ ይዞ ገብቶ ለአዶንጎ አቀብሎት በመከነችው ሙከራ የተነቃቁት ባለ ሜዳዎች በመጀመርያዎቹ 20 ደቂቃዎች በርከት ያሉ ሙከራዎችም ማድረግ ችለው ነበር።  በተለይም ወግደረስ ታየ አክርሮ መቶ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡት እና እንየው ካሳሁን መትቶ በረከት ሳሙኤል ተደርቦ ያወጣው ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች ነበሩ።

ሁለቱ የድሬ አጥቂዎች ማለትም በረከት ይሳቅ እና ሀብታሙ ወልዴ በብዙው የጨዋታው ክፍለ ግዜ ከሁለቱ የወልዋሎ ተከላካዮች ተለጥፈው እና ብዙ እንቅስቃሴ ባለማረጋቸው የድሬ አጥቂዎች ከወልዋሎ ተከላካይ ክፍል ጀርባ ያለው ሰፊ ክፍተትም መጠቀም አልቻሉም። በዚህም ዮሴፍ ዳሙዬ ከርቀት አክርሮ መቶ ዮሃንስ ሽኩር ካዳነው ሙከራ ውጭ በመጀመርያው አጋማሽ ለጎል የቀረበ ሙከራ አላረጉም። ጨዋታው ቀስ በቀስ  እየቀዘቀዘ ሄዶ ሙከራ ሳያስተናግድ ለረጅም ደቂቃ ቆይቶ በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች ወልዋሎዎች በከድር ሳልህ እና ሪችሞንድ አዶንጎ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። እንየው ካሳሁን አሻምቶ አዶንጎ በግንባሩ ገጭቶ ወልዋሎን መሪ ማድረግ ቢቃረብም ሳምሶን በማይታመን ሁኔታ ጎል ከመሆን አድኖታል። ከዚ በተጨማሪም መኩርያ ደሱ አሻምቶት ከድር ሳልህ ያመከነውም ተጠቃሽ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ እንግዶቹ ድሬዎች በተሻለ መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ጫና ፈጥረው መጫወትም ችለው ነበር። በረከት ተሰማ በረጅሙ የተላከውን ኳስ ለማውጣት በሚዘልበት ወቅት አልፋው በመሄዷ ሐብታሙ ወልዴ ሊያገኛት ጥረት ቢያደርግም ዮሃንስ ወጥቶ አድኗታል። እንዲሁም ማናየ ፋንቱ በማዕዘን ምቱ መምቻ አካባቢ ያገኛትን ኳስ በግሩም ሁኔታ አልፎ ለወግደረስ ሰጥቶ ወግደረስ ሳይጠቀምባት የቀረችው ተጣቃሾች ነበሩ።

ከዛ በኋላ በሜዳው በዘነበው ከባድ ዝናብ ሜዳው በውሀ በመሞላቱ ጨዋታው በ63ኛው ደቂቃ ለመቋረጥ ተገዷል። ነገ 04:00 ላይም ከተቋረጠበት ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል። ጨዋታው በነበረበት አቻ ውጤት ከተጠናቀቀ ወይም ወልዋሎ ድሬዳዋ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲወርድ ድሬዳዋ የሚያሸንፍ ከሆነ በሊጉ የሚቆይ ይሆናል።