ኤፍሬም አሻሞ ወልዋሎን ተቀላቅሏል

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ኤፍሬም አሻሞን የክረምቱ 6ኛ ፈራሚ አድርጓል።

በ2008 ክረምት ንግድ ባንክን ለቆ ወደ ደደቢት ያመራው ኤፍሬም አሻሞ ከጅማ አባጅፋር ጋር በተደረገ ጨዋታ በተመለከተው የቀይ ካርድ ምክንያት ክለቡ እገዳ አስተላልፎበት የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ጨዋታዎችን ሳይጫወት መቅረቱ የሚታወስ ሲሆን የሁለት ዓመት ውሉን ማጠናቀቁን ተከትሎ ከደደቢት መልቀቂያውን መቀበሉ ታውቋል።  የኤፍሬም ወደ ወልዋሎ ማምራት በፕሪንስ ሰቨሪንሆ ላይ ተንጠልጥሎ የታየው የመስመር ማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ አማራጭ እንደሚፈጥር ይጠበቃል። 

የክለብ እግርኳስን በሐረር ቢራ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ደደቢት የመራው ኤፍሬም ከደደቢት በፊት በነበረባቸው ክለቦች አብሯቸው ከሰራው አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያም ጋር በወልዋሎ በድጋሚ የሚገናኝ ይሆናል። 

በደደቢት የቡድን አጋሮቹ የነበሩት ብርሀኑ ቦጋለ እና ክሌመንት አዞንቶን ተከትሎ ወደ ዓዲግራት የተጓዘው ኤፍሬም አሻሞ ታናሽ ወንድሙ ብርሀኑ አሻሞ ጋርም በአንድ ቡድን የሚገናኝ ይሆናል።